ቦንጋ፤ መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዘንድሮ የበልግ አዝመራ 359 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚለማ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
የ2017 ዓ/ም ክልላዊ የበልግ አዝመራ የበቆሎ ክላስተር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በጊምቦ ወረዳ ተካሂዷል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው እንደገለፁት በክልሉ የበልግ አዝመራ በሰፊው የሚከናወን ሲሆን በዘንድሮም 359 ሺህ ሄክታር ማሳ በተለያዩ ሰብሎች ይለማል።
በዚህም ዋና ዋና ሰብሎችን ጨምሮ ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግና ከሚለማው አጠቃላይ ማሳ ውስጥ 30 በመቶውን በክላስተር በማልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በዛሬው እለትም በጊምቦ ወረዳ ሾምባ ሼካ ቀበሌ ክልላዊ የኩታ ገጠም እርሻ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር መከናወኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የቀበሌው አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደነበረ ያነሱት አቶ ማስረሻ አሁን ላይ መሻሻል እንዳለ ገልፀዋል።
የክልሉ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፣ ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ከዚህ ቀደም ጦም ያደረ መሬት እንዲታረስ፣ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲቀርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ በመስኖ የማልማት ልምዱ እንዲዳብር በተሰራ ስራም ውጤት እየመጣ መሆኑን ገልፀው ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ከተለመደው አሰራር በመላቀቅ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ ማሳን መንከባከብና ምርትን በወቅቱ መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
የግብርና ባለሙያዎች አርሶ አደሩን በማንቃትና በማነቃቃት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አቶ ፍቅሬ አሳስበዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በዞኑ የበልግ አዝመራ ውጤታማ እንዲሆን ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮ የበልግ አዝመራ 95ሺህ 951 ሄክታር መሬት በማልማት ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋዎ አባመጫ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይም የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025