የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

በክልሉ የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን የማሳደግ ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው

Apr 10, 2025

IDOPRESS

መቀሌ፤ ሚያዚያ 1/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል በውሃ ዕቀባ እና የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን የማሳደግ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ በዘንድሮው መኸር በሄክታር በአማካይ 21 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አበራ ከደነው ለኢዜአ እንደተናገሩት የውሃ ዕቀባ ስራዎችን በማከናወን የዝናብ እጥረት ችግርን ከመከላከል ባሻገር የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን የማሳደግ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በውሃ ዕቀባ ስራው አብዛኞቹ የክልሉ አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን እርጥበትን የማቀብ ዘመቻውም እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ/ም እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የእርሻ ፓኬጅ ዝግጅትና አጠቃቀም እንዲሁም የማስፈፀም አቅምን ማጎልበት የሚያስችል ስልጠና ለሁሉም ባለሙያዎች እና አርሶ አደሮች በመስጠት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመኸር ወቅት ከአንድ ሄክታር መሬት በአማካይ 21 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ የእርሻ ዝግጅት እና ግብዓት አቅርቦት እየተሟላ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር እንዲሁም የእርሻ ትራክተሮች ከወዲሁ ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከፌደራል መንግስት ወደ ክልሉ እስካሁን የተጓጓዘውን ከ150 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ወረዳዎች የማዳረስ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመኸር ወቅት 16 ሚሊዮን ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያና ኮምፖስት ጥቅም ላይ ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

በ2017/18 የምርት ዘመን በክልሉ 758ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 16 ሚሊዮን ኩንታል ለመሰብሰብ ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.