መተማ ፤ ሚያዚያ 1/2017(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን የእጣንና ሙጫ ምርትን በጥራትና በብዛት ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አካባቢና ደን ጥበቃ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በጽሕፈት ቤቱ የአካባቢ የህግ ተከባሪነትና የማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ አድጎ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዞኑ ከፍተኛ የሆነ የእጣንና ሙጫ ምርት የሚያስገኝ የደን ሀብት አለው።
በዞኑ በደን ከተሸፈነ 760 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ውስጥ ከ234ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው የእጣንና ሙጫ መሆኑን በማሳያነት ገልጸዋል።
በአካባቢው ያለውን እምቅ የእጣንና ሙጫ ሃብት በመጠቀም በበጀት ዓመቱ እስካሁን 800 ኩንታል የሚጠጋ እጣንና ሙጫ በማምረት በማዕከላዊ ገበያ በኩል ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን አስታውቀዋል።
ተጠቃሚነትን ለማስፋትም ወጣቶችን በዘላቂ የደን አስተዳደር ልማትና ጥበቃ ማህበራት በማደራጀት ሃብቱን በመጠበቅና በማምረት ላይ እንዲሰማሩ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የደን ይዞታውን በጠበቀ መልኩ ለማምረት 35 ማህበራትና 11 ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን ቡድን መሪው ጠቁመዋል።
በተለይ የእጣን ዛፍ በተደጋጋሚ ለማምረት በሚደረግ ጥረት በቀላሉ የሚጎዳ በመሆኑ በአመራረትና በአያያዝ ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በመተማ ወረዳ በለምለም ተራራ በማህበር ተደራጅተው እጣን እያመረቱ ካሉት መካከል አቶ እሸቱ ኢብራሂም በሰጡት አስተያየት፤ ደኑን በመጠበቅ ማልማትና መጠቀም መቻላቸውን ተናግረዋል።
የእጣን ዛፉ እንዳይጎዳና ዘላቂ ምርት እንዲሰጥ በመጠበቅና በመንከባከብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አውስተው፤ በዚህ ዓመት ከ200 ኩንታል በላይ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በየዓመቱም እጣንና ሙጫ አምርተው በመሸጥ ለእያንዳንዳቸው እስከ 60ሺህ ብር የሚደርስ ገቢ እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቴዎድሮስ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ግብይት ማህበራት ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ክንዱ ወርቁ በበኩላቸው፤ የእጣንና ሙጫ ሀብትን ለሀገር ኢኮኖሚ በሚጠቅም መንገድ ለማምረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የተመረተባቸው አካባቢዎችን እረፍት በመስጠት ዛፉ እንዳይጎዳ ለማድረግ የሚያስችል ስልጠና ለአባል ህብረት ስራ ማህበራት እንደሚሰጥ አብራርተዋል።
ዩኒዬኑ በቀጣይ ራሱን ችሎ የእጣንና ሙጫ ምርትን ወደ ውጭ በመላክ ከሚያገኘው ገቢ አባል ማህበራትን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ባለፈው ዓመት ሰባት ሺህ 137 ኩንታል የእጣን እና ሙጫ ምርት ለገበያ በማቅረብ ከ175ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን ከአካባቢና ደን ጥበቃ ጽሕፈቱ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025