የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ህይወት እና ጉዞ

ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት አስፈላጊው የታሪፍ ማስማማት ስራ ተከናውኗል - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

Apr 10, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት አስፈላጊው የታሪፍ ማስማማት ስራ መከናወኑን የንግድ እና ቀጣዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር "ቀጣናዊ ትስስር እና አለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ለንግድ ዘርፍ እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ የ2017 በበጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ አካሂዷል።


የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ከእቅድ በላይ የተፈጸመበት ነው።

ይህም ምቹ የንግድ ከባቢን መፍጠር በመቻሉ መሆኑን ተናግረዋል።

በኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፊቃድ ለ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተገልጋዮች አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸው፤ አፈጻጸሙ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 722 ሺህ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

በበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት ከወጭ ንግድ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን ጠቅሰው፤ በወጭ ንግድ የተገኘው ውጤት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው መሆኑን አመላክተዋል።

በበጀት አመቱ መጨረሻ ከ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከወጭ ንግድ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም የዘርፉን አፈጻጸም ከፍ ያደረጉ ከ 25 በላይ መመሪያዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ከቅዳሜ እና እሁድ ገበያ አንጻርም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 374 ተጨማሪ ገበያዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸው፤ የዋጋ ግሽበትን በመከላከል ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና በተያያዘም የታሪፍ ማስማማት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ስትራቴጂ መዘጋጀቱንና ይህም በመጽደቅ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እንዲሁም ለትግበራው አስፈላጊው የታሪፍ ማስማማት ስራ መጠናቀቁን እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እነዚህ ከጸደቁ በኋላም የሙከራ ንግድ የመጀመር ጥረቶች እንደሚደረጉም አመላክተዋል።

በበጀት አመቱ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማጠናከር በቀጣይ የላቀ ውጤት ለማምጣት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.