ባህርዳር፤ ሰኔ 11/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በ2017/2018 የምርት ዘመን የታቀደውን የሰብል ልማት ለማሳካት የእርሻ ስራውን በትራክተር በመታገዝ ጭምር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ያረሱትን መሬት በዘር ከመሸፈን በተጓዳኝ የእርሻ ስራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን አርሶ አደሮች ገልጸዋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ባለሙያ ኤልያስ በላይ፤ በምርት ዘመኑ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለማልማት ታቅዶ የእርሻና የዘር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ለኢዜአ ተናግረዋል።
የእርሻ ስራው በትራክተር ጭምር በመታገዝ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከታቀደው ውስጥ እስካሁን 497ሺህ 437 ሄክታሩ ታርሶ ቀድሞ በሚዘራ የበቆሎ፣ ገብስ፣ ዳጉሳ፣ ማሽላ፣ ጥራጥሬና የቅባት ሰብል ዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።
ቀሪውን መሬት በቀጣይ እንደየዘር ወቅቱ የእርሻ መሬቱን በማለስለስ በዘር የመሸፈኑ ተግባር በማጠናከር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ቀድሞ የደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን ጠቅሰው፤ የበቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴና ሌላውንም የሰብል ዓይነት ጨምሮ ከተዘጋጀው 200ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ውስጥ 83ሺህ ኩንታል ለአምራቹ መድረሱን ተናግረዋል።
ቀሪው የግብርና ግብዓትን ጥቅም ላይ ለማዋል በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በምርት ዘመኑ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በማልማት ከ187 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ከወዲሁ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ባለሙያው አስረድተዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የደብረ ኤልያስ ወረዳ አርሶ አደር እንዳላማው ቢሻው በሰጡት አስተያየት፤ ከላቸው ሶስት ሄክታር የእርሻ መሬት ውስጥ አንዱን ሄክታር አርሰው በበቆሎ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል።
ቀሪውን ሁለት ሄክታር መሬት በጤፍ፣ ዳጉሳና ስንዴ ሰብል ዘር ለመሸፈን የእርሻ ስራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን አመልክተው፤ በግብዓትነት የሚውሉ ሶስት ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ገዝተው ጥቅም ላይ እያዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ካላቸው መሬት ውስጥ አንድ ሄክታር የሚጠጋውን አርሰው በዘር መሸፈናቸውን የተናገሩት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን የወንበርማ ወረዳ አርሶ አደር ቸኮል ታደለ ናቸው።
የማዳበሪያ አቅርቦቱ መልካም መሆኑን ጠቁመው፤ ቀሪ መሬታቸውን በስንዴና በርበሬ የሰብል ዘር ለመሸፈን የእርሻ ስራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን አመልክተዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ነዋሪው አርሶ አደር ካሳሁን መንግስት በበኩላቸው፤ የአፈር ማዳበሪያ ወቅቱን ጠብቆ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።
ይህንን በመጠቀምም አንድ ሄክታር መሬታቸውን አርሰው በገብስ ዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025