አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2017(ኢዜአ)፦ትውልድ በመቅረጽ ሂደት ውስጥ ሚና ያላቸው ተቋማት የሥራ ባህል እንዲዳብር ትውልድን የማነጽ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
"የስራ ባህል ምርታማነት ለሀገር ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ተካሄዷል፡፡
በመድረኩም የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር)፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፣ የፌዴራል እና ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት እንዳሉት፤ የስራ ባህል ግንባታ ስኬታማ እንዲሆን ትውልድን ከታች ጀምሮ መቅረጽ ይገባል፡፡
ትውልድን በመቅረጽ የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች ፣መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ ሊሆን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ለሙያ ያለን አመለካከት የአስተሳሰብ ለውጥ የሚፈልግ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከቤተሰብ ጀምሮ የስራ ባህልን የማዳበር ስራ ትኩረት እንደሚፈልግ ጠቅሰዋል፡፡
ያሉንን አቅምና ጸጋ መለየት በዚያ ላይ ተመስርቶ ፈጠራና ፍጥነትን በማከል ውጤታማ ስራ ማከናወን ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
በዚህ ረገድ እንደ አገር መልካም ጅምሮች በመኖራቸው ይህንኑ በማስፋት ለውጤት እንዲበቃ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ላይ ያሉ ባለድርሻ አካላትም ሚናቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል የተጀመረው አገራዊ ጥረት የሚሳካው ሁሉም ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ መሆኑን አመልክተዋል።
ለዚህ ደግሞ መሰል የውይይት መድረክ ፋይዳው ብዙ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሐሰን ሁሴን (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ልምዳቸውን እና ካፒታላቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያመጡ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በውጭ ያሉ ዜጎች በኢትዮጵያ የሚኖራቸው ተሳትፎ ከፍ እንዲል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ሕዝብ መምህርና ተመራማሪ እሸቱ ጉርሙ(ፕሮፌሰር) እንዳሉት፤ ምርታማነትን ለማሳደግ በትምህርትና በክህሎት የበለጸገ የሰው ኃይል ማፍራት ይጠይቃል።
በእውቀትና በአስተሳሰብ የተገነባ ትውልድ ውጤታማ ነው ያሉት ተመራማሪው፤ ሙያን መሰረት ያደረጉ የሥራ ሥምሪት ጉዳዮች የበለጠ ትኩረት ይሻሉ ብለዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር አማካሪ ጥላሁን በጅቷል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከጠባቂነት የተላቀቀ አስተሳሰብ ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸው፤ በምርቶች ላይ እሴት መጨመር ጉዳይ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።
ያሉንን ዕድሎች ተጠቅመን መለወጥ አለመቻላችን ሊያስቆጨን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በፖሊሲ ጥናት ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ጥላሁን ተፈራ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘው አገራዊ ግብ የሚሳካው የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት በማስፈን ውስጥ ነው።
ለዚህም እንደ መንግሥት የተጀመሩ ሥራዎችን አበረታች መሆናቸውን ገልጸው፤ መሰል ሥራዎችን ማስፋት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025