የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ኢትዮጵያ ለጀመረችው ራስን የመቻል ጉዞ አንዱ ማሳኪያ መንገድ ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

Jun 23, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2017(ኢዜአ)፦ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ኢትዮጵያ ለጀመረችው ራስን የመቻል ጉዞ አንዱ ማሳኪያ መንገድ በመሆኑ በርካታ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ ሲሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ፡፡

የኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ ዲግሪ (ሌቭል 6) እና በሁለተኛ ዲግሪ (ሌቭል 7) ያሰለጠናቸውን ሁለት ሺህ ተማሪዎችን አስመርቋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በመርሃ ግብሩ እንደገለጹት፤ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ወሳኝ ነው።

መንግስት ዘርፉን በማጠናከር ዓለም የደረሰበት ደረጃ ለማድረስ ባለፉት አመታት በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አንስተዋል።

ይህንን ተከትሎ ዘርፉ አለም አቀፍ ተቀባይነት ማግኘቱን አመልክተው፤ በ2017 የአለም አቀፍ የክህሎት ህብረተሰብ አባል መሆን የተቻለበት ውጤታማ አመት መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉ ኢትዮጵያ ለጀመረችው ራስን የመቻል ጉዞ ወሳኝ በመሆኑ በቀጣይ የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በቀጣይ አመት በሌቭል 8 የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው፤ ይህም ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ያስችላል ነው ያሉት።

ተመራቂ ተማሪዎች በሰለጡኑበት ዘርፍ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በታታሪነት እንዲያገለግሉ ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።


የኢፌደሪ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰጣቸውን ስልጠናዎች እያሳደገ ይገኛል ብለዋል።

በዛሬው እለትም በመጀመሪያ ዲግሪ 1 ሺህ 880 በሁለተኛ ዲግሪ 120 በአጠቃላይ ሁለት ሺህ ተማሪዎች በቂ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና በመውሰድ ለምረቃ መብቃታቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይ በሰባት አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገበው የዋንጫ ተሸላሚ የሆኑት ተማሪ ባንቴ ዘላለም እና ሃብታም ሞላ በዚሁ ግዜ በትምህርት ቆይታቸው በንድፈ ሃሳብና በተግባር የታገዘ ትምህርት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡


በቀጣይም በተማሩበት ዘርፍ ስራ ሳይጠብቁ ስራ ፈጣሪ በመሆን ለሌሎች የስራ እድል ለመፍጠር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የዳን ቴክኖክራፍት መስራች ኢንጂነር ዳንኤል መብራቱ በቴክኒክ እና ሙያ ክህሎት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሙያ ክብር ሽልማት ተበርክቷላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.