የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ወደ 14ሺህ የሚጠጉ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ማላቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል

Jul 4, 2025

IDOPRESS

ሰቆጣ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦ በዋግ-ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር 14ሺህ የሚጠጉ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን በዘላቂነት ከተረጂነት ማላቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን የብሔረሰብ አስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት አስታወቀ።


''ፅህፈት ቤቱ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት'' በሚል መሪ ሃሳብ በ2017 በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን የሚገመግም የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል።


የብሔረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይሉ ግርማይ በመድረኩ እንዳሉት የተጀመረው ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ሃገራዊ ንቅናቄ በዞኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በምግብ ራስን ለማስቻል ፋይዳው የጎላ ነበር።


በዚህም በዞኑ 13 ሺህ 849 የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን በዘላቂነት ከተረጅነት እንዲላቀቁ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።


ተረጂዎች የአካባቢያቸውን ፀጋ ተጠቅመው በማልማት በራስ አቅም በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።


ለዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ለማላቀቅ የተከናወኑ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ተግባሩ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።


የብሔረሰብ አስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በተደረገው ጥረትም 13 ሺህ 849 እማና አባወራዎች ለምረቃ በማብቃት በዘላቂነት ከተረጂነት የማላቀቅ ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።


ከሴፍቲኔት ፕሮግራም ተመርቀው ለመውጣት የተዘጋጁት በአነስተኛ ንግድና በመስኖ ልማት ዘርፍ ተሰማርተው ሃብትና ጥሪት በማፍራታቸው እንደሆነም አመልክተዋል።


''ቀሪዎቹም 2018 ዓ/ም ከተረጅነት እንዲላቀቁ እየተሰራ ነው'' ያሉት አቶ ምህረት የአካባቢን ፀጋ ተጠቅመው በማልማትና ራሳቸውን በመቻል ከተረጂነት እሳቤ እንዲወጡ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።


''በወረዳው የሚገኙ 1ሺህ 363 የሴፍትኔት ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ለማላቀቅ የጀኔሬተርና የቀጥታ ገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል'' ያሉት ደግሞ የአበርገሌ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት የምግብ ዋስትና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደሳለኝ ማሞ ናቸው።


በወረዳው የእርሻ መሬታቸው መስኖ ገብ ለሆኑ 200 የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች በነፍስ ወከፍ የጄኔሬተር ድጋፍ ተደርጎላቸው ማልማት መጀመራቸውን ገልፀዋል።


የሰቆጣ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት የሴፍቲኔት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተስፉ ተገን፤ በወረዳው በሴፍቲኔት ይረዱ የነበሩ 1 ሺህ 405 እማና አባዎራዎች ራሳቸውን ችለው ከተረጂነት እንዲወጡ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።


በዚህም ለእያንዳቸው 33ሺህ 300 ብር የመቋቋሚያ ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በንግድና በእንስሳት እርባታ እንዲሰማሩ የክህሎት ስልጠና እንደተሰጣቸውም አስረድተዋል።


በብሔረሰብ አስተዳደሩ 151 ሺህ 638 የህብረተሰብ ክፍሎች በሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈው ከተረጂነት እንዲወጡ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑም ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


በሰቆጣ ከተማ ዛሬ በተካሄደው ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የንቅናቄ መድረክም አመራሮች፣ የምግብ ዋስትናና የግብርና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.