የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በምዕራብ አርሲ ዞን በ97 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቦሎቄ እየለማ ነው

Sep 30, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዳማ ፤ መስከረም 19/2018(ኢዜአ)፡-በምዕራብ አርሲ ዞን በ97 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቦሎቄ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱላሂ ቤከን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች ቦሎቄን ጨምሮ የጥራጥሬ ሰብሎች ልማት በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።

በተለይም በሻሸመኔ፣ አርሲ ነገሌ፣ ቆሬ፣ ሻላና ሄበን አርሲ ወረዳዎች ላይ ለወጪ ንግድ የሚሆን ቦሎቄ በስፋት እየለማ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩ በራሱ ማሳ ላይ ከሚያለማው ቦሎቄ ባሻገር ከባለሃብቶች ጋር የውል እርሻ በማስገባትና አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም በማደራጀት እያለማ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በገቡት ውልና ትብብር መሰረት የቦሎቄ ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ ቴክኖሎጂና የሜካናይዜሽን አገልግሎትን ጨምሮ የተሟላ የግብርና ኤክስቴንሽን ድጋፍ ለአርሶ አደሮቹ እየተሰጠ ቦሎቄን በተሻለ ደረጃ እያለሙ ይገኛሉ ብለዋል።

በአጠቃላይ በዞኑ በቦሎቄ ከሚለማው 97 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 57 ሺህ ሄክታሩ በውል እርሻ እንዲታቀፍ ተደርጎ ሰብሉ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ኃላፊው ተናግረዋል።

በቆላማ የዞኑ ወረዳዎች አርሶ አደሩ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲያመርት ድንችን ጨምሮ የአፈር ለምነትን የሚጠብቁ የአትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች እየለሙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በዚህም አርሶ አደሩ ምርታማነቱ እንዲጨምርና አማራጭ የገቢ ምንጭ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በቦሎቄ ልማት ከተሸፈነው መሬትም 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የሚጠበቅ መሆኑንም ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።

በዞኑ አርሶ አደሮች በግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ አቅምን ማሳደግና ተኪ ምርቶችን ማምረት ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.