የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶች ስኬታማ እንዲሆኑ የአመራሩን አቅም የማጎልበቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

Sep 30, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ጋምቤላ፤ መስከረም 19/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶች ስኬታማ እንዲሆኑ የአመራሩን አቅም የማጎልበቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ከብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በየደረጃው ለሚገኙ የክልሉ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ መስጠት ጀምሯል።


ርዕሰ መስተዳድሯ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንዳሉት በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተገኙትን የልማት ስኬቶች ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የአመራሩን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም የማጎልበቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ባለፉት ዓመታት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ስኬታማ የልማት ድሎች የተመዘገቡት በአመራሩ ዘንድ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት መገንባት በመቻሉ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በክልሉ የታለሙ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን ስኬታማ ለማድረግ የአመራሩን የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የሚያጎለብት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እየተሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና ዋና ዓላማም ክልላዊ ብሎም ሀገራዊ ኃላፈነትን በብቃት የሚወጣ አመራርን ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።

ስለሆነም የስልጠናው ተሳታፊ አመራሮች የለውጡን ጉዞ ለማሳለጥ ታስቦ የሚሰጠውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በትኩረት መከታተል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።


የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ እንዳሉት የጋምቤላ ክልል ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋዎች ያሉበት አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል ።

በተለይም ክልሉ ለግብርና ልማት የሚመች ስነ-ምህዳር፣ የማዕድን፣ የቱሪዝምና ሌሎችም የተፈጥሮ ጸጋዎች የታደለ አካባቢ መሆኑን ገልጸው፤ ይኸንን ሀብት መጠበቅና ማልማት ከተቻለ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለሀገር እድገት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ሀብቱን በአግባቡ የማስተዳደር ዘይቤና እሴት ጨምረው የማልማት ክህሎትን ማዳበር ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.