🔇Unmute
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ከማስጠበቅ የሚመነጭ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ገለጹ።
ምክትል ሰብሳቢው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በተፈፀመባት ታሪካዊ ስህተትና ኢ-ፍትሐዊ ሁኔታ የባሕር በር አልባ ከሆኑ ሀገሮች መካከል አንዷ ለመሆን ተዳርጋለች።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት የምትገኝና የብዙ ሕዝብ ባለቤት ሀገር መሆኗ የባህር በር ከሌላቸው ሀገራት የተለየ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።
በዓለም የንግድ ሥርዓት በሸቀጦች እንቅስቃሴ ግዙፍ ስፍራ በሚሰጠው የቀይ ባሕር ላይ የባህር በር ማጣት በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ኪሳራው ብዙ መሆኑን አስረድተዋል።
የባሕር በር ባለመኖሩ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የገቢና ወጪ የንግድ ሥርዓት ለከፍተኛ ወጪ እንድትጋለጥ ማድረጉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር አልባነትም የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት በገቢና ወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትና በዜጎች ኑሮ ላይ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ሥርዓት ውስጥ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የባሕር በርና የወደብ አገልግሎት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የግዙፍ ኢኮኖሚና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለቤት እንዲሁም ለቀይ ባህር በቅርብ ርቀት የምትገኝ መሆኗ የባሕር በር ፍትሐዊ ጥያቄዋ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳና የህልውና ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የባሕር በር መሻቷም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ተጠቃሚነትን ከማሳለጥ የሚመነጭ፣ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትና ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስርን በማሳለጥ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነትን ከማስጠበቅ ጋር የተቆራኘ ጭምር መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ትስስርም የንግድ ልውውጥና የቱሪስት ፍሰትን በማጠናከር የቀጣናውን ዜጎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማሳደግ የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን በመርህ ላይ የተመሰረተ የባሕር በር ጥያቄም ለጋራ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ሰላምና ደህንነት የሚኖረውን ገንቢ ሚና በመገንዘብ የቀጣናው ሀገራት ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት እውን ለማድረግ የውስጥና የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አብራርተዋል።
ዜጎችም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ለማስገኘት በሚደረገው ጥረት ሁሉ የድርሻቸውን ገንቢ ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025