የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

 በአማራ ክልል ሃይል ቆጣቢ የኢነርጂ አማራጮችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ  ለማድረግ  እየተሰራ ነው

Oct 31, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ባሕር ዳር፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ 250 ሺህ ሃይል ቆጣቢ የኢነርጂ አማራጮችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ጥላሁን ሽመልስ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ለገጠርና ከተማ ማሕበረሰብ የሀይል አማራጭ ማቅረብ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ይህም ለምግብ ማብሰያ፣ ለመብራትና ሌሎች የሃይል አቅርቦትን ለማሟላት የሚያስችሉ ሃይል ቆጣቢ የቴክኖሎጂ አማራጮች ላይ በማተኮር እንደሆነ ገልጸዋል።

የሀይል አማራጮቹ የኢነርጂ አቅርቦት ችግርን ከመፍታት ባሻገር የማሕበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ወደ ዘመናዊነት የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም በተያዘው የበጀት ዓመት 100 ሺህ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች፣ 90 ሺህ በፀሐይ ሃይል የሚሰራ ቴክኖሎጂ እና 60 ሺህ ሃይል ቆጣቢ የኤሌክትሪክ ምጣዶችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም ተጠቃሚዎችን ከመለየትና አቅራቢዎችን ከማደራጀት ባለፈ 15 ሺህ ሃይል ቆጣቢ ምድጃዎች ማሰራጨት መቻሉን ጠቅሰዋል።


እንዲሁም 6 ሺህ በፀሐይ ሃይል የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች በማሰራጨትም ዜጎች በአነስተኛ ወጪ የሀይል አማራጮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግም የብድር አማራጭ የማመቻቸቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በቀሪ ወራትም ዕቅዱን በተሟላ መንገድ ለማሳካት ከመንግስት በተጨማሪ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና ማሕበረሰቡን በማደራጀት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሃይል ቆጣቢ የኢነርጂ አማራጮች ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ ባሻገር ለማገዶ የሚውል የደን ሃብቱ ጉዳትን በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የቢሮው ምክትል ሃላፊ አብራርተዋል።

በ2017 የበጀት ዓመትም በክልሉ ከ306ሺህ በላይ ሃይል ቆጣቢ የኢነርጂ አማራጭ ቴክኖሎጂዎች ለሕብረተሰቡ መሰራጨታቸውን ከውሃና ኢነርጂ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.