🔇Unmute
ወልቂጤ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፦የጉራጌ ማህበረሰብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መከወኛ "ጀፎረ" ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር መተሳሰሩ የአካባቢውን የቱሪስት መስህብነት እያሳደገው መምጣቱን የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለጸ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት በስፋት ተግባራዊ ከሆነባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የጉራጌ ዞን አንዱ ነው።
ልማቱ የዞኑን አርሶ አደር አኗኗር ከማዘመን ባለፈ ለዓመታት ባህሉ አድርጎ ሲጠቀምበት የቆየውን ''ጀፎረ''ን የቱሪስት መስህብ እንዲሆን እያስቻለ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ጀፎረ የጉራጌ ማህበረሰብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ከጥንት ጀምሮ የሚከውንበት ሲሆን ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተሳስሮ እንዲለማ መደረጉ የቱሪስት መስህብነቱ ይበልጥ እንዲጨምር አድርጓል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ጀፎረን ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር አቀናጅቶ ለማልማት የተሰጠው ትኩረት ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልፀዋል።

ልማቱ አካባቢውን ውብና ይበልጥ ሳቢ ከማድረግ ባለፈ በተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉን ጠቅሰው፣ በዚህም በአካባቢው በአገልግሎት ሰጭነት የተሰማሩ ተቋማት ገቢያቸው ማደጉን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ላጫ ገለጻ የገጠር ኮሪደር ልማቱ የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር በኩልም የጎላ ሚና እየተጫወተ ነው።
በቀጣይም ማህበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም ሀብት በማድረግ ለገቢ ምንጭነት ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ በበኩላቸው፤ ጀፎረን ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ከገጠር ኮሪደር ልማት በተጨማሪ የአካባቢው ሰላምና የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት በየጊዜው የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰው፣ ይህን ወደ ማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለገጠር ኮሪደር ውጤታማነት የማህበረሰቡ ተሳትፎ የጎላ መሆኑንም ወይዘሮ መሰረት ጠቅሰዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡት በዞኑ የእኖር ወረዳ ነዋሪ አቶ ትዕግስቱ ሃብቴ እና አርሶ አደር መሃሙድ ያሲን የገጠር ኮሪደር ልማት የአካባቢያቸውን ገጽታ መቀየሩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች ወደአካባቢው እንዲመጡ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በገጠር ኮሪደር ልማት ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እንዳነሳሳቸው የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ልማቱ ከጀፎረ ጋር እንዲተሳሰር መደረጉ የጎብኚዎችን ቀልብ ይበልጥ ለመሳብ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በተለይ ውብ የገጠር መንደሮች፣ በአካባቢው የሚከወኑ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች፣ መንደሮችን ተከትለው የተሰሩ ባህላዊ ቤቶች፣ የእንሰት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶች የጎብኚዎችን ቀልብ እንደሚስቡም አስረድተዋል።
ለቱሪስቶች መስህብ እየሆነ የመጣው የገጠር ኮሪደር ልማት ለአካባቢው ማህበረሰብም የገቢ ምንጭ እንዲሆን በትኩረት መስራት እንደሚገባም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025