🔇Unmute
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፦መንግሥት ቱሪዝምን አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ያደረገው ከዓለም ሀብት ለመቋደስና ሀገራዊ ጥቅምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር" በሚል ርዕስ በቱሪዝም ዘርፍ ዙሪያ ከኤን ቢ ሲ ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ልዩ ቆይታ፣ ዘርፉ ያለውን ስትራቴጂካዊና ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እንዲሁም ከአምስቱ የኢኮኖሚ አምዶች አንዱ የሆነበትን ምክንያት አብራርተዋል።
መንግሥት የያዘው ትልቅ ራዕይ የበለጸገች፣ የተለወጠችና የተከበረች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ታላቅ ሕልም ለማሳካት በአጭር ጊዜ ውስጥ አስተማማኝ ምላሽ ሊሰጡ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ሰፊ ጥናትና ምክክር ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በግብርና ላይ ብቻ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት ስትሞክር መቆየቷን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)፤ ሆኖም ግብርናው ራሱ በበቂ ደረጃ ማደግ ባለመቻሉና ሌሎች ዘርፎችን ማንቀሳቀስ ባለመቻሉ የተፈለገው ውጤት እንዳልተገኘ አስረድተዋል።
በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ጥገኝነት ያለው አካሄድ ሀገርን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማበልጸግ እንደማያስችል በመረዳት፣ አንዱ ለሌላው ግብዓት የሚሆንበትና እርስ በርሱ የሚሰናሰል የብዝሃ-ዘርፍ አካሄድ መከተል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ከመንግሥት አምስት ዋና ዋና የትኩረት ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ ሆኖ መውጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
ቱሪዝም ለምን ዋነኛ የትኩረት ዘርፍ እንደሆነ ሲያብራሩም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ የሚንቀሳቀሰው የሀብት መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ያስረዳሉ።
በዓለም ዙሪያ ዘርፉ 12 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቀስ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንደ አሜሪካ 215 ቢሊዮን ዶላር፣ ስፔን 107 ቢሊዮን ዶላር፣ ታይላንድ 95 ቢሊዮን ዶላር እና ከአፍሪካ ግብፅ እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያገኙ አብራርተዋል።
ከዚህ ሀብት ኢትዮጵያና አፍሪካ ምን ያህል ማግኘት አለባቸው? የሚለው ቁልፍ ጥያቄ መሆኑን በማንሳት፣ ይህንን እምቅ የዓለም ሀብት ኢትዮጵያ መቋደስ መቻሏ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን በጥሩ ሁኔታ ለማገዝ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የጎብኚዎችን ፍሰት ያነጻጸሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዓመት ፈረንሳይ እስከ 102 ሚሊዮን፣ ሜክሲኮ ወደ 97 ሚሊዮን፣ ማሌዥያ ከ39 እስከ 40 ሚሊዮን፣ እንዲሁም በአፍሪካ ሞሮኮ ከ19 እስከ 20 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚጎበኟቸው ጠቅሰዋል።
ይህም ለሀገራት ኢኮኖሚ ዕድገትና የኢኮኖሚ አቅም ከፍተኛ ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ቱሪዝም ያለውን የገበያ አማራጭ ሲያብራሩ፤ ምርትን በኮንቴይነር አሽጎ ወደ ውጭ ሀገር ከመላክ ይልቅ፣ ሸማቹን ቱሪስት በቀጥታ ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት ያለ ተጨማሪ የማሸግና የትራንስፖርት ድካም ዝግጁና ቀጥተኛ የሀገር ውስጥ ገበያ የመፍጠር ትልቅ አቅም እንዳለው አስገንዝበዋል።
ቱሪስት ወደ ሀገር ሲመጣ እውቀት እንደሚያመጣ፣ እንደሚሸምት፣ እንደሚዛመድና ኢንቨስት እንደሚያደርግ በመግለጽ ዘርፉ ለሌሎች መስኮችም ያለውን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የስራ ዕድል ችግር ለመቅረፍም የቱሪዝም ሚና የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ቱሪስቶች ወደ ሀገር ውስጥ ሲመጡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ምግብ፣ ልብስና ቅርጻቅርጽ ሸምተው ስለሚሄዱ የኢንዱስትሪ ምርት በቀጥታ ገበያ እንዲያገኝ ያደርጋል ነው ያሉት።
ይህም አጠቃላይ የሸቀጥ ገበያና የንግድ ልውውጥ እንዲነቃቃ ከማድረጉ ባለፈ፣ እንደ ጫማ ማፅዳትና ቡና ማፍላት ላሉ አነስተኛ ቢዝነሶች ጭምር ሰፊ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ዘርፉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸው፥ ቱሪስት ሲመጣ ክፍተቶችን አይቶ ለመሙላት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንደሚስብም ገልጸዋል።
በመሠረተ ልማት በኩል ከቱሪዝም የሚገኘው ሀብት ፓርኮችንና መዳረሻዎችን ለመንከባከብ፣ ለመጠገንና አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን ለመጨመር ትልቅ ዕድል እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ድንቅ ታሪካዊ ሀገር መሆኗን በማንሳት፥ ዘርፉ ብሔራዊ ትዕምርቶችን ለማብዛት፣ ሕዝቦች ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው ሲንቀሳቀሱና ሲጎበኙ አንዱ የሌላውን መልካም ነገር አይቶ እንዲያደንቅና እንዲማር በማድረግ ሀገራዊ ፍቅርን፣ እውቀትንና መዋሃድን እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
መንግሥት ቱሪዝምን ከአምስቱ ቁልፍ ዘርፎች መካከል አንዱ አድርጎ የወሰደው ይህንን የዓለም አቀፍ ሀብት ለመቋደስና ሀገራዊ ጥቅምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ጋምቤላ፤ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት...
Sep 4, 2026
አሶሳ፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ተኪ ምርቶችን የማምረት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ ...
Sep 3, 2026
ሆሳዕና፤ ነሀሴ 5/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዜጎችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት መመዝገ...
Aug 12, 2026
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ)፦የመንግሥት በሙስናና ሕገ ወጥ ድርጊት የተሰማሩ አካላትን በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ርምጃ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ኢዜአ...
Aug 12, 2026