🔇Unmute
አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን በሪፎርም ሥራ በትርፋማነት፣ በጭነት እና በመንገደኞች ማጓጓዝ ከፍተኛ እምርታ ማስመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በመደበኛ ጉባኤው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ያቀረቡትን የ2019 ዓ.ም የመንግሥት ዕቅድ መነሻ በማድረግ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም በውጭ ዜጎች በማኔጅመንት ኮንትራት ይተዳደር የነበረ ሲሆን፣ የተጀመሩ ሥራዎችንም ለማጠናቀቅ በቂ ፋይናንስ አልነበረም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ማስተዳደር የቻለች ሀገር የባቡር ኮርፖሬሽንን ማስተዳደር እንዴት ይሳናታል በሚል በተከናወነ የሪፎርም ሥራ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገደማ ትርፍ ያስገኝ የነበረው ኮርፖሬሽን አሁን ላይ 43 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስገኘት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በሪፎርሙ በተመዘገቡ ውጤቶች መካከልም ቀደም ሲል የኤሌክትሪክና የነዳጅ ሎኮሞቲቮች 11 ገደማ የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ወደ 36 የሚጠጉ ሎኮሞቲቮች መያዝ ማቻሉን ተናግረው ጋሪዎች ከ560 ገደማ ወደ ከ1 ሺህ በላይ ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል።
በዓመት 198 ሺህ መንገደኛ ያስተናግድ የነበረው ኮርፖሬሽን ዛሬ 588 ሺህ ሰው ማስተናገድ ላይ መድረሱን ጠቅሰው የካርጎ ትራንስፖርት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ወደ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን አድጓል ብለዋል።
የባቡር ፍጥነት በሰዓት ከ37 ኪሎ ሜትር ወደ 55 ኪሎ ሜትር ማሳደግ መቻሉን አንስተው ከቡና ኤክስፖርት ቢያንስ 95 በመቶ የሚሆነው እና ከማዳበሪያ ኢምፖርት 25 በመቶ ገደማ የሚጠጋው በባቡር እየተከናወነ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
እንዲሁም ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ እና ከኮምቦልቻ እስከ ሐራ ገበያ ያሉ የባቡር መስመሮችን ቀሪ ሥራዎች በውስጥ አቅም ለማከናወን ባለፈው ዓመት አጋማሽ ገደማ ተጀምሮ ሰፊ እምርታ መታየቱን ጠቁመዋል።
በተለይ ከአዋሽ ወደ ኮምቦልቻ በሚወስደው መስመር መተሐራ አካባቢ ከአንድ ዓመት በፊት በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ ድልድዮች መፍረሳቸውንና አንዳንድ መስመሮችን ቦኖ መውሰዱን አስታውሰው፣ እነዚህን ጨምሮ እስካሁን 100 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ሥራ መጠናቀቁንና ቀሪውን ሥራ እስከ አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት በፊት በውጭ ማኔጅመንት ይተዳደር በነበረበት ወቅት በሚገኘው ገቢ ዕዳ መክፈል ቀርቶ የሠራተኛ ደመወዝ መክፈል የማይቻልበት ሁኔታ እንደነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ቀይሮ በራስ አቅም መገንባትና ማስተዳደር መቻሉ ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሮቤ ህዳር 09/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን የተፈጥሮ፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ የጎብኝዎች ቁጥርና የዘርፉ ገቢ እ...
Nov 19, 2026
ሆለታ፤ ህዳር 07/2019 (ኢዜአ)፦ የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር የፈለቁ 214 የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማድረስ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት...
Nov 17, 2026
ጭሮ ህዳር 5/2019 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ካላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር አንፃር ከባሕር በር ውጪ ሆና መቀጠል አይገባትም ...
Nov 16, 2026
አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የኮፕ 32 ጉባኤን በምትዘጋጅበት ወቅት፣ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የአደጋ ቅድመ ዝግጁነትና እርምጃዎችን የትኩረ...
Nov 12, 2026