🔇Unmute
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):-በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተያዘው ዓመት የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግና የውጭ ምርቶችን በመተካት አምስት ቢሊዮን ዶላር ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ79.4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውና የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነውን ዘመናዊውን የሀማሳ ሞዴል መንደር ዛሬ በይፋ መርቀዋል።

መንደሩ የኢትዮጵያ የገጠር ማኅበረሰብን ሕይወት ከባህላዊ አኗኗር ወደ ዘመናዊ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑ ተመላክቷል።
ሀማሳ የተሰኘውን ይህንን ዘመናዊ መንደር መርቀው የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ስራው በአገሪቱ የገጠር ማሻሻያ ረገድ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ መንደር በተለይ የገጠሩን ነዋሪ የኑሮ ደረጃና ክብር ከፍ ለማድረግ ታቅዶ የተሰራ ሲሆን፣በአንድ ግቢ ውስጥ ዘመናዊ የንጽህና መጠበቂያዎችን፣ የተደራጀ የቤት እንስሳት ማቆያን፣ በባዮ ጋዝ የሚሰራ የሃይል አቅርቦትን እንዲሁም የተሟላ የጓሮ ግብርናን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ ንጽህና እና የተመጣጠነ ምግብ ወሳኝ መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች በማሟላት የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ማገዝ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።

የዚህ ዘመናዊ መንደር ግንባታ ትልቁ ስኬት፣ሙሉ ወጪው የተሸፈነው በመንግሥት ሳይሆን በአካባቢው አርሶ አደሮች መሆኑ ነው።
ባለፈው ዓመት መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች የሞዴል ቤቶችን በመስራት መንገድ ካሳየ በኋላ፣ዘንድሮ ነዋሪዎቹ እራሳቸው ተነሳሽነቱን ወስደው የራሳቸውን መኖሪያዎች መገንባታቸውን ነው ያብራሩት።
በዚህም አርሶ አደሮቹ ከመንግሥት የተሰጣቸውን ስልጠናና ሙያዊ እገዛ ብቻ በመጠቀም፣ በገዛ ጓሯቸው አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ማር፣ ዓሳና የዶሮ እርባታን በማስፋፋት የራሳቸውን የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ መቻላቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች በራሳቸው ግቢ ውስጥ ይሄንን መሰል ምርታማነት ማምጣት መቻላቸው በኑሮ ላይ የሚፈጠሩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ጠቁመዋል።
መንግሥትም ይህንን በአርሶ አደሩ የተጀመረውን አበረታች የልማት ተሞክሮ ወደሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋትና ይበልጥ ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በጋሞ ዞን የ'ዮ ሆልዲንግ’ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካን ጎብኝተዋል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ከሰሎች ከውጭ ሀገር ይገባ እንደነበር አስታውሰው እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የሚደርስ ውጪ እንደሚወጣ አመልክተዋል።
አሁን በኢትዮጵያ ከሰል በሀገር ውስጥ እንደሚመረት እና ለኢንዱስትሪ ግብአት እንደሚውል አመልክተዋል።
የተለያዩ የከሰል ማምረቻ ፋብሪካዎችም ተመርቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸውንና ይህም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሙላት ባለፈ ለውጭ ገበያ የማቅረብ እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
በተያዘው ዓመት ኢንዱስትሪው በሀገር ውስጥ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት አምስት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን አመልክተዋል።
በአጠቃላይ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ):-በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተያዘው ዓመት የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግና የውጭ ምርቶችን በመተካት አምስት ቢሊዮን ዶላር ...
Jul 4, 2026
አዳማ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ቡናን ከመደበኛ ወቅት በተጨማሪ በበጋ መስኖ በማልማት የአምራቹን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መደ...
Jun 17, 2026
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣዮቹ 90 ቀናት የከተማዋን ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ላ...
Jun 17, 2026
ሀዋሳ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ ሀዋሳ ከተማን በማልማት የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ማዕከልነቷን ይበልጥ ለማሳደግ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚ...
Jun 14, 2026