የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

ኢትዮጵያ በግብርና እና ታዳሽ ኃይል እያሳየች ያለው ፈጣን እድገት የሚደነቅ ነው 

Mar 23, 2026

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እና ታዳሽ ኃይል ልማት ላይ እያሳየች ያለው ፈጣን እድገት የሚደነቅ ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የባንግላዲሽ አምባሳደር ኤር ቫይስ ማርሻል ሲትዋት ናይም ገለጹ።

ባንግላዲሽ በዘርፉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላትም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተተገበሩ የግብርና ምርታማነት ኢንሼቲቮች አስደማሚ ውጤት እያስገኙ ነው

ኢትዮጵያ ለግብርና ምርታማነት ምቹ በሆኑ ሥነ-ምህዳራዊ ሁኔታዎች የታደለች በመሆኗ፣ ግብርናን በተለይም ስንዴን በኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዋ ማዕከል እያደረገች ትገኛለች ብለዋል።

ሀገሪቱ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የመስኖ ልማት መስፋፋት፣ የተሻሻሉ የዘር ሥርዓቶች እና ሰፊ ንቅናቄን በመተግበር ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሚደነቁ እመርታዊ ለውጦችን አስመዝግባለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መርሃ ግብርን በሰፊው በማስጀመር የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በዚህም ሀገሪቷ በስንዴ ራስን ከመቻል ባለፈ ወደ ውጭ በመላክና ለቀጠናው የግብርና ትራንስፎርሜሽን አርአያ እየሆነች ነው ብለዋል።

የስንዴ ልማት ስኬት ታሪክ የኢትዮጵያን ሰፊ የልማት ርዕይ የሚያሳይ ዋነኛ ማሳያ ሆኖ ብቅ ያለ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ መንግሥትም ልምዱን ለምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ለማካፈል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከግብርና ባለፈ ኢትዮጵያ ወደ ታዳሽ ኃይል ለመሸጋገር የያዘችውን ትልቅ ዓላማ ያደነቁት አምባሳደሩ፤ ይህም ለታዳጊ ሀገራት በአርአያነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ንጹሕ ኃይልን የልማት ስትራቴጂዋ ማዕከል አድርጋለችም ብለዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን በንፋስ እና በፀሐይ ኃይል የሚከናወኑ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት የኃይል አማራጮቿን እያሳደገች እንደምትገኝም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል አየር ንብረት ለውጥን በሚመለከት ባንግላዴሽ እና የአፍሪካ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸውን የጋራ ተጋላጭነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ታዳጊ ሀገራት ለአየር ብክለት ያላቸው አስተዋጽኦ አነስተኛ ቢሆንም ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ከፍተኛ ተጋላጭ በመሆናቸው ይህንን ኢ-ፍትሐዊነት ለመቀየር በዓለም አቀፍ መድረኮች የጋራ ድምፃቸውን ሊያጠናክሩ ይገባልም ብለዋል።

በመሆኑም የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስና ለጋራ መጻኢ ዕድል ተጨባጭ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተገቢው ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.