የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

ድርጅቱ የብዙኃነት አቅም ያለው በመሆኑ ይህን አቅም ወደ ስትራቴጂያዊ ጥቅም ማምጣት ያስፈልጋል

Mar 31, 2026

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት የብዙኃነት አቅም ያለው በመሆኑ ይህን አቅም ወደ ስትራቴጂያዊ ጥቅም ማምጣት እንደሚያስፈልግ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አስገነዘቡ።

11ኛው የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ በማላቡ ኢኳቶሪያል ጊኒ እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባኤው እየተሳተፋ የሚገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ድርጅቱ የብዙኃነት አቅም ያለው በመሆኑ ይህን አቅም ወደ ስትራቴጂያዊ ጥቅም ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል።

ተለዋዋጭ በሆነው የአለም የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ውስጥ የአባል ሀገራቱን ጥቅም የሚያስከብር ጠንካራ ድርጅት ሆኖ መቀጠል እንዳለበትም በአፅንኦት ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በንግግራቸው ለድርጅቱ ጥንካሬ ይበጃሉ ያላቸውን ሀሳቦችም አካፍለዋል።

በዚህም ድርጅቱ የብዙኃነት አቅም ያለው በመሆኑ ይህን አቅም ወደ ስትራቴጂያዊ ጥቅም ማምጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት።


ለዚህም የደቡብ - ደቡብ ግንኙነትን ማጠናከር ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ያሉ ሲሆን መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢኮኖሚን ከገነቡ ሀገራትና ድርጅቶች ጋር ያለን ግንኙነት ከቀደመው የእርዳታ ሰጭ እና ተቀባይ ግንኙነት ወደ የጋራ ተጠቃሚነት ለማሸጋገር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የድርጅቱ አባል ሀገራት ተመሳሳይ የባለቤትነት ስሜትን ማዳበር እንዳለባቸውም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።

ቀጣይነት ያለው ልማት ማረጋገጥ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባትና ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን መስራት የአባል ሀገራት የጋራ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት አባል ሀገራት ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ያላቸው ሚና ከተጠቃሚነት ወደ ፈጣሪነት(አምራችነት) መሸጋገር እንዳለበትም ተናግረዋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ሳይበር ደህንነት እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ጉዳይ በልዩ ትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ባስመዘገበቻቸው ውጤቶች ቀጣዩን የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (ኮፕ 32) እንድታስተናግድ መመርጧን አስታውሰዋል።

ይህም የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት በመገንባት ሂደት ያላቸውን ተሞክሮ የሚያቀርቡበት ትልቅ ዕድል እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው ሶስቱም ቀጣናዎች የጎላ አስተዋጽኦ ባላደረጉበት የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገዱ መሆናቸውን አንስተዋል።

የአየር ንብረት ፍትህ እንዲረጋገጥ የተባበረ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በጉባኤው አፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ክልሎችን የወከሉ መሪዎች ንግግር ያደረጉ ሲሆን አፍሪካን በመወከል የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር እና የቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ኤቫሪስት ንድዪሺሚዬ መልእከት አስተላልፈዋል።

የድርጅቱን የፋይናንስ ምንጭ ቀጣይነት ማረጋገጥ፣ የድርጅቱን መዋቅራዊ አሰራር ማጠናከር እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጋራ አቋም መያዝ በጉባኤው ጎልተው የተሰሙ ድምፆች መሆናቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።

በማላቡ ኢኳቶሪያል ጊኒ እየተካሄደ የሚገኘው 11ኛው የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ እስከ ነገ መጋቢት 20/2018 ዓም ድረስ ይቆያል።

በጉባኤው ከሶስቱም ክልሎች የሚገኙ የሀገራት መሪዎች እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.