🔇Unmute
ባህርዳር፤ ሰኔ 28/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የእርሻ ምርት ግብዓት ቁጥጥርን በማጠናከር ምርታማነትን ለማላቅ በተከናወነ ተግባር ውጤት መገኘቱን የክልሉ የግብርና ጥራትና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ።
የክልሉ የግብርና ጥራትና ቁጥጥር ባለሥልጣን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድና አፈፃፀም መድረክን በባህር ዳር ከተማ ዛሬ አካሄዷል።
በወቅቱም የአማራ ክልል የግብርና ጥራትና ቁጥጥር ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ፈንታሁን ስጦታው እንደገለጹት፤ ባለሥልጣኑ በዘር፣ በማዳበሪያ፣ በፀረ-አረም ኬሚካል፣ በመጤ አረምና በሌሎች የግብርና ግብዓቶች ላይ የጥራትና ቁጥጥር ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም በክልሉ የእርሻ ምርት ግብዓት ቁጥጥርን በማጠናከር ምርታማነትን ለማላቅ በተከናወነ ተግባር ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ከ10 ሺህ 800 ሄክታር በላይ በምርጥ ዘር በተሸፈነ መሬት ላይ ቁጥጥር በማድረግ፣ ከ600 ሄክታር በላይ የተዘራው ዘር የጥራት ደረጃውን ባለማሟላቱ ውድቅ መደረጉን አንስተዋል።
በተለይም በመሰብሰብ፣ በማከማቸት፣ በማጓጓዝና በማሰራጨት ላይ የሚከሰትን የጥራት መጓደል ለመቀነስ ለባለድርሻ አካላት ሰፊ ግንዛቤ ተፈጥሮ ወደ ሥራ በመገባቱ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ግብርና ጥራትና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኔ ገብሬ በበኩላቸው ሥራው በምሥራቅ አማራ በሚገኙ በዋግ ኸምራና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደሮች፣ በሰሜንና በደቡብ ወሎ ዞኖች ላይ በማተኮር መሠራቱን ገልጸዋል።
በነዚህ ዞኖች በዘር ብዜት ላይ የተሰማሩ ስምንት ድርጅቶች ላይ ከማሳ ጀምሮ ተገቢውን የዘር ጥራትና ቁጥጥር በማድረግ፣ ከ20 ሺህ ኩንታል በላይ ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
በቀጣይም የግብዓት ጥራት፣ ደህንነትና ቁጥጥር ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው በክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለወጪ ንግድና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ምርት ለማምረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ጥራቱ የተረጋገጠ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩና ለባለሀብቱ በወቅቱ ማቅረብ ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ማደግ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የሚመረተውን ምርጥ ዘር ወደ ውጭ ለመላክና ለማስገባት፣ በሥርዓተ ምግብ በኩልም የሰውን ጤና የማይጎዳ ምርት ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ለማቅረብ እንደሚያስችል አስረድተዋል።
በዚህም ባለሥልጣኑ የግብርና ግብዓትን ጥራት በማሳ ላይና በላቦራቶሪ በመመርመር እንዲሁም የላቀ ቁጥጥር በማድረግ እያከናወነ ያለው ሥራ የሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የባለሥልጣኑ እና የዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
አዳማ፤ጳጉሜን1/2018(ኢዜአ)-መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የኦሮ...
Sep 7, 2026
ጅማ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ):- ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ወደ መስኖ ልማትና ሜካናይዜሽን እየተደረገ ያለው ሽግግር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ አዲስ ምዕራፍ...
Sep 3, 2026
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጥጥ ልማትን በጥራትና በብዛት በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ...
Aug 28, 2026
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር በምርምር፣ በሰው ሃይል ልማት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር...
Aug 21, 2026