🔇Unmute
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦የአፍሪካን የልማትና ኢንቨስትመንት አድማስ ለማስፋት ተዓማኒ መረጃና ዘመናዊ የስታቲስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ዋና ጸሐፊ ክሌቨር ጋቴቴ ገለጹ።
የአፍሪካ ስታቲስቲክስ ኮሚሽን 10ኛ ጉባኤና የተባበሩት መንግሥታት የጂኦስፓሻል መረጃ አስተዳደር ኮሚቴ ለአፍሪካ 12ኛ ጉባኤ የጋራ የመክፈቻ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የሩዋንዳ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ዕቅድ ሚኒስትር ዩሱፍ ሙራንግዋና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክሌቨር ጋቴቴ ተገኝተዋል።
በተጨማሪም ፖሊሲ አውጪዎች፣ የስታቲስቲክስ ባለሙያዎች፣ የልማት አጋሮችና የመረጃ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ዋና ጸሐፊ ክሌቨር ጋቴቴ በዚህ ወቅት፤ የመረጃና ስታቲስቲክስ አለመሟላት መንግሥታት በሚያከናውኗቸው የልማት ሥራዎች ላይ እንቅፋት ይፈጥራል ብለዋል።
በዚህም መረጃንና የስታቲስቲክስ ሥርዓትን ከሪፖርት ባሻገር ውሳኔዎችንና የልማት ሥራዎችን በሚመራ አግባብ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሀገራትም የ2030 የሕዝብና ቤት ቆጠራን በመጠቀም ከብሔራዊ መታወቂያ፣ ከሲቪል ምዝገባ፣ ከንግድ ምዝገባና ከአድራሻ መለያዎች ጋር የሚያገናኝ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የአፍሪካን የልማት እውነታ የሚያሳይ መረጃ ማዘጋጀት ያስፈልጋል ያሉት ዋና ጸሐፊው፤ የሥራ አጥነት፣ የሥራ ጥራትና የድህነት መጠን ልኬትም የልማት ተነሳሽነትን ለመተግበር ይረዳል ብለዋል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎትና አዳዲስ የመረጃ ምንጮችን በጥንቃቄ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የስታቲስቲክስን ወቅታዊነት ቢያሻሽሉም፣ ባልተሟላ መረጃ የሰለጠኑ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቶች የተሳሳተ ውጤት ሊሰጡ እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ሀገራት ብሔራዊ የስታቲስቲክስ ቢሮዎችም የማረጋገጫና የሚስጢራዊነት ጥበቃ ደረጃዎችን በማውጣት እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
የስታቲስቲክስና የጂኦስፓሻል መረጃን በማቀናጀት መንግሥታት ለሰው ሠራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦችን በመለየት እንዲመሩ ያግዛል ብለዋል።
በአስተማማኝ የስታቲስቲክስና የኢኮኖሚ መረጃ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግና የባለሀብቶችን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ እንደሚረዳ አክለዋል።
በቂ ኢንቨስትመንት ሳይኖር ተዓማኒ መረጃ ማግኘት እንደማይቻል ገልጸው፣ መንግሥታት ለቆጠራ፣ ለመሠረተ ልማትና ለሠራተኞች የሚያስፈልግ በቂ በጀት እንዲመድቡ ጠይቀዋል።
ኢሲኤ በአፍሪካ የስታቲስቲክስ ማዕከሉ በኩል ከብሔራዊ የስታቲስቲክስ ቢሮዎች ጋር በመሥራት ለስታቲስቲክስ ሥርዓቶች በቂና ዘላቂ ፋይናንስ እንዲኖር ከመንግሥታትና ከልማት አጋሮች ጋር እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ደብረ ብርሃን ፤ ጥቅምት 9/2019 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ ከ76 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱ...
Oct 20, 2026
ጎንደር ፣መስከረም 28/2019 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በመካናይዜሽን የታገዘ ዘመናዊ ግብርና ለማስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን በምክትል ርእስ መስተዳድር ማእረግ የ...
Oct 9, 2026
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል የሚገነባው የዳመርጆግ-ደወሌ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ...
Sep 30, 2026
ገንዳውኃ፣ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- የእጣንና ሙጫ ደኖችን በመንከባከብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የማህበረሰብ አቀፍ የጥበቃ ሥራዎች እየተካሔደ መ...
Sep 20, 2026