የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ለማሳደግ ዲጅታል አገልግሎትን ማስፋትና የኮንትሮባንድ ቁጥጥርን ማጠናከር ይገባል-ቋሚ ኮሚቴው

Jul 1, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦የገቢዎች ሚኒስቴር ገቢ የመሰብሰብ አቅሙን ለማሳደግ ዲጅታል አገልግሎትን ማስፋትና የኮንትሮባንድ ቁጥጥርን ማጠናከር እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ሚኒስቴሩ በበኩሉ በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 815 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የገቢዎች ሚኒስቴር የገቢው ዘርፍ የ2017 በጀት አመት የ11ወራት አፈፃፀምን ገምግሟል።

የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ከሀገር ውስጥ ታክስ እና ከወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ ከ900 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል።


እስካሁን ባሉት የበጀት ዓመቱ 11 ወራት 815 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉንም ነው ያብራሩት።

በወጪና ገቢ ኮንትሮባንድ ላይ በተደረገው የቁጥጥር ስራ 19 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉንም ተናግረዋል።

የሚኒስቴሩንና የጉሙሩክ ኮሚሽንን አሰራሮች የሚያዘምኑ የተለያዩ ዲጂታል የቴክኖሎጂ አሰራሮችን ማልማትና ወደስራ እንዲገባ መደረጉንም ገልፀዋል።

የስነምግባር ጉድለት የታየባቸው 405 ሰራተኞች ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ስንብት የሚደርስ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ በወንጀል እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ መሰራቱንም አስረድተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በቀጣይ በጀት ዓመት ከዘንድሮ ብልጫ ያለው ገቢ ለመሰብሰብ በመታቀዱ ይህን ለማሳካት እንዲሁም የታክስ ገቢ እድገትን ለማረጋገጥ ምን እየተሰራ ነው የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ልዩ የደረሰኝ ህትመት ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ችግርና የኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድረው ህገወጥ ኬላዎች ላይ ምን እየተሰራ ነው የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ በሰጡት ማብራሪያ በበጀት ዓመቱ ቀጣይነት ያለውና የአገር ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የተያዘውን የገቢ እቅድ ለማሳካት እቅዱ በተገቢው ትንተና ላይ ተመስርቶ መሰራቱንና የዲጂታል አማራጮችን መተግበር አስቻይ ሁኔታ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑንም ተናግረዋል።

የታክስ አስተዳደር ውጤታማነትን የሚያሳድጉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ነው ያብራሩት።

በደረሰኝ የሚስተዋሉ ማጭበርበሮችን ለመከታተል እንዲያመች በኪውአር ኮድ(QR CODE) የተደገፈ ደረሰኝ ወደስራ ለማስገባት ከአሳታሚ ድርጅት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

700 ሺህ የእጅ በእጅ ሽያጭ ደረሰኝ ህትመት ለማድረግ ታስቦ ወደ ስራ ቢገባም ፍላጎቱ በሶስት እጥፍ ያደገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚሁ መሰረት የአሳታሚውን ድርጅት አቅም የማሳደግ ስራ እየተሰራ ከመሆኑ ባለፈ ወደ ዲጂታል የደረሰኝ አገልግሎት ለመግባት እየተሰራ ነው ብለዋል።


የጉሙሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አዝዘው ጫኔ በበኩላቸው፥ ህገወጥ ኬላዎች በወጭና ገቢ ንግድ ስርዓቱ እንዲሁም በሀገራዊ ገቢ ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማስቀረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉሙሩክ ኮሚሽን በአገሪቱ ገቢ ላይ ትልቅ ሚና ያላቸው መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የፕላን፣በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ ናቸው።

የማስፈፀም አቅምን ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ስራ መሰራቱና የታክስ ስርዓትና የህግ ተገዢነት በማሳደግ በኩል የተከናወነው ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

የቴክኖሎጂ አሰራሮችን ለማልማትና ለመጠቀም እንዲሁም ምቹ የስራ ከባቢን ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራትንም በጥንካሬ አንስተዋል።

የ11 ወራት የገቢ አፈፃፀሙም የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው፥ የታክስ ስርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከርና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.