የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

በዓሉ የክልሉን ባህልና የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል

Nov 28, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ሆሳዕና፤ ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ 20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የክልሉን የባህልና ቱሪዝም ሀብቶች በማስተዋወቅ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ዕድል እንደሚሰጥ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ፡፡

በየዓመቱ ህዳር 29 የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችንና ህዝቦች ቀን በዓል መላው ኢትዮጵያን በአንድነት ባህላዊ እሴትና ማንነታቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበትና በጋራ በመድመቅ የኢትዮጵያን የተለያየ መልክ የሚያጎሉበት ነው።

ዘንድሮም በዓሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ለ20ኛ ጊዜ "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ፤ በዓሉ የክልሉን የቱሪዝም ሀብት ለማስተዋወቅ ካለው ፋይዳ አንጻር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፣ የበዓሉ መከበር የክልሉን የባህልና ቱሪዝም ሀብቶች በማስተዋወቅ ከዘርፉ ጥቅም ለማግኘት እድል ይሰጣል።

በሆሳዕና ከተማና አካባቢው በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሀብቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ የበዓሉን አጋጣሚ በመጠቀም የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችንና ባህላዊ ሀብቶችን የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በበዓሉ ለመታደም ወደ ክልሉ ለሚገቡ እንግዶች ያሉትን የቱሪዝም ሀብቶች፣ የተለያዩ ብሔሮችን ባህል፣ ታሪክና እሴቶች ለማስተዋወቅ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

ለእዚህም አስጎብኚ ማህበራትን፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችንና የባህል አልባሳት ማምረቻና መሸጫ ማህበራትን ከማደራጀት በተጨማሪ በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶች በክልሉ ያሉ የተለያዩ ብሄሮችና ብሄረሰቦችን ባህልና ታሪክን ከማስተዋወቅ ባለፈ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር ጭምር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።


በሆሳዕና ከተማ የሲና አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት ወጣት ሌሞወርቅ ሀይለማርያም በበኩሏ፤ 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በክልሉ መከበሩ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት እንደሚፈጥር ገልጻለች፡፡

በክልሉ በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ የመስህብ ስፍራዎች እንደሚገኙ ጠቅሳ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን ጭምር ለበዓሉ ታዳሚዎች ለማስተዋወቅ መዘጋጀታቸውን ተናግራለች፡፡

በሆሳዕና ከተማ የኪታ እደ ጥበብና ባህላዊ አልባሳት ማምረቻና መሸጫ ባለቤት ዲዛይነር መስከረም ገብሬ ኢትዮጵያውያን ዘርፈ ብዙ መገለጫዎች ያለን ህዝቦች ነን ስትል ገልጻለች፡፡


የብሔር ብሔረሰቦች መገለጫ የሆኑ ባህላዊ አልባሳትን በተለየ ቀለምና ዲዛይኖች በማዘጋጀት ለበዓሉ ለሚመጡ እንግዶች ለማስተዋወቅ ዝግጅት ማድረጓን ተናግራለች።

በዚህም የበዓሉ ታዳሚ እንግዶች ሆሳዕናን እንዲያስታውሱና አይረሴ ትዝታ እንዲኖራቸው ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑን ነው የገለጸችው።

በዓሉ "ዴሞክራሲያዊ መግባባት፣ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በክልሉ አስተናጋጅነት በሆሳዕና ከተማ ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.