የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

ኢትዮጵያ እና ቻይና በግብርና በተለይም በቡና ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እያሳደጉ ነው

Jan 9, 2026

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቻይና በግብርና በተለይም በቡና ዘርፍ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ አጋርነትና ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እያሳደጉ መሆኑን የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

ቻይና የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ በመሆን ባለፉት አምስት ዓመታት ከ33ኛ ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ ማለቷ ታውቋል።

የኢትዮጵያን ቡና በቻይና እና በዓለም ገበያ የማስተዋወቅ ዓላማ ያለው የንግድና የኢኮኖሚ ትብብር በቻይና ጁጆ ከተማ ተካሂዷል።

የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ እና ቻይና በግብርናው ዘርፍ ያላቸው ትብብር ከንግድ ባለፈ ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

ለዚህ ትብብር መጠናከርና ለቡና ወጪ ንግድ ዕድገት መነሻ ከሆኑት መካከልም የቻይና የቡና መዳረሻነት ማደግ፣ የነፃ ታሪፍ ዕድል፣ የቴክኖሎጂ እና የዕውቀት ሽግግር፣ የኢ-ኮሜርስ ትስስር እንዲሁም የሁናን ግዛት የንግድ ማዕከልነት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡


የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ መንግሥት የግብርና ምርቶችን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ለዚህም የምርት ጥራትንና መጠንን ለማሳደግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን፣ አዳዲስ ኢኖቬሽኖችንና የግብርና ግብዓቶችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቻይና የተካሄደው ኮንፍረንስም የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

ከቡና ምርት ባለፈ የእንስሳት ተዋጽኦን፣ የዓሳ ምርቶችንና ሌሎች የግብርና ውጤቶችን በስፋት ቻይናን ጨምሮ ወደ ሌሎችም ሀገራት ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ጠቁመው፤ ለኢትዮጵያ ላኪዎች አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለቡና ምርታማነትና ጥራት የሰጠችው ትኩረት በዘርፉ የወጪ ንግድ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ቡና በበርካታ ሀገራት ተመራጭነቱ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ በተለይም ቻይና ዋነኛ የቡና መዳረሻ እየሆነች ነው ብለዋል።

ለአብነትም ቻይና ከአምስት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ቡና የወጪ ንግድ መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት መካከል ከነበረችበት 33ኛ ደረጃ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ማለቷንም ተናግረዋል፡፡

ይህ ውጤት የተመዘገበው በአንድ በኩል የቻይናውያን የቡና ፍላጎት መጨመር በሌላ በኩል የቻይና መንግሥት ለአፍሪካ ሀገራት በሰጠው የነፃ ታሪፍ ዕድል የተነሳ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና በቻይናውያን ዘንድ ተወዳጅነትን እያተረፈ መምጣቱንም ጨምረው ጠቅሰዋል።

የሁለቱ ሀገራት የቡና ንግድ ትስስር እያደገ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቅርቡ በጁጆ ከተማ በተካሄደው ኮንፍረንስ በርካታ ገዥ ኩባንያዎች መሳተፋቸውንና አዳዲስ የገበያ ትስስር ስምምነቶች መፈረማቸውን ገልጸዋል፡፡


የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ በቻይና የተካሄደው ኮንፍረንስ የኢትዮጵያን ቡና በስፋት ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።

ቻይና ያላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና በየጊዜው እያደገ የመጣው የቡና ፍላጎት ለኢትዮጵያ ቡና ወደፊትም ሰፊና አስተማማኝ የገበያ መዳረሻ እንድትሆን ያደርጋታል ነው ያሉት።

በመድረኩ ከቡና አፈላል ጀምሮ ያለውን ኢትዮጵያዊ ሥርዓት ለቻይናውያን ማስተዋወቅ መቻሉን ጠቅሰው፤ ቡና በሀገር ገጽታ ግንባታ በኩል ያለውን ትልቅ አቅም ለመጠቀም እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቡና ንግድ ትብብር ይበልጥ ለማስፋት አዲስ ምዕራፍ መከፈቱንም አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.