የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

በአራተኛው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ከ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ስምምነት እንደሚደረግ ይጠበቃል

Mar 4, 2026

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፦በአራተኛው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ስምምነት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው

አራተኛው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ የኢንቨስትመንት ፎረም መጋቢት 17 እና 18 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ፎረሙን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የዓለም ባንክ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።


የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ፎረሙ በኮሚሽኑ፣ በገንዘብ ሚኒስቴርና በአጋር የልማት ድርጅቶች ትብብር የተዘጋጀ ነው።

የመድረኩ ዋና ዓላማ አዳዲስ የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ፣ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ማሳየት እንዲሁም በቅርቡ የተደረጉ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለባለሀብቶች ማስተዋወቅ ነው ብለዋል።

በፎረሙ ላይ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ታዋቂ ኩባንያዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ አማካሪዎችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል፡፡

በአራተኛው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ከሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ስምምነት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዕድሎች በማስተዋወቅና የፎረሙን ስኬት በማብሰር ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው፤ መንግስት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ሰፊ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችን ማድረጉን ገልጸዋል።


በኢትዮጵያ ባሉ እምቅ አቅሞችና በመንግስት የሪፎርም ስራዎች ምክንያት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ መነሳሳት መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ይህ ፎረም በእነዚህ ዕድሎች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ትልቅ መድረክ እንደሚሆን አስረድተዋል።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ የደቡብ ሱዳንና ሱዳን ዳይሬክተር ሜርየም ሳሊም፤ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ አቅም በመጥቀስ በፎረሙ ለመሳተፍ አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው ብለዋል ።


ወጣትና እያደገ ያለ የሰው ኃይል መኖሩ፣ ስትራቴጂካዊ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ፣ ጠንካራ የግብርና መሠረትና እየሰፋ ያለ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለኢትዮጵያ ተመራጭነት እንደ ምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በተስፋ ብቻ ሳትወሰን በተግባር የሚታዩ የሪፎርም እርምጃዎችን እየወሰደች በመሆኑ ሜርየም ሳሊም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ የኢንቨስትመንት ፎረም ከ800 በላይ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች፣ የንግድ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የልማት አጋሮች እንደሚታደሙበት ተገልጿል።

በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና እና ግብርና ነክ ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን እና ታዳሽ ሀይል፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (ICT) እና ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲሁም በቱሪዝም እና ሆቴል ዘርፎች ላይ ያተኮሩ የጎንዮሽ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ተገልጿል።

በተጨማሪም ከፍተኛ የፖሊሲ እና ኢንቨስትመንት የውይይት መድረኮች እንዲሁም የተመረጡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እና የልማት ኮሪደሮች የመስክ ጉብኝቶች እንደሚካሄዱ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.