🔇Unmute
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ባለፉት 10 ወራት ከወጪ ንግድ 8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) በግብርና ምርቶች የኤክስፖርት ቢዝነስ እንዲሁም በቡና ቅምሻና ደረጃ አወጣጥ ዘርፍ ለሦስት ወራት ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ዘመናዊና ውጤታማ የወጪ ንግድ ሥርዓት ለመገንባት በዕውቀትና በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል ማፍራት ወሳኝ ነው።
በዚህም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አካዳሚ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ አበረታች ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በወጪ ንግድ አስደናቂ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ በተለይም በያዝነው የ2018 በጀት ዓመት አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት 10 ወራት ከወጪ ንግድ 8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረው እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ደግሞ ገቢውን ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የዛሬዎቹ ሰልጣኞች ይህንን ሀገራዊ የገቢ ግብ ለማሳካትና የወጪ ንግዱን በዕውቀትና በክህሎት ለመምራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖራቸውም አመላክተዋል።
ተመራቂዎቹም ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምሰሶ ሆነው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መርጊያ ባይሳ በበኩላቸው፤ የወጪ ንግድ በዘመናዊ ግብይት ሥርዓት፣ በዕውቀትና በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የወጪ ንግድ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ጥራት ያለው ምርት ለገበያ ማቅረብ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም ለወጪ ንግድ ስኬት ቁልፍ በሆኑት የደረጃ አወጣጥና የጥራት ቁጥጥር ስልጠናዎች በምርት ገበያ አካዳሚ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
አካዳሚው ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በቡና ቅምሻ ዘርፍ ብቻ ከ3ሺህ 200 በላይ ሰልጣኞችን አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት በግብርና ምርቶች ኤክስፖርት ቢዝነስ እና በቡና ደረጃ አወጣጥ 168 ባለሙያዎች ማስመረቁን አስታውቀዋል።
የምርት ገበያው አካዳሚ እያስመዘገበ ያለው ስኬት ከሀገር ውስጥ አልፎ አህጉራዊ እውቅናን እያገኘ መምጣቱን የገለጹት አቶ መርጊያ፣ እስካሁን ከ8 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የአካዳሚውን ተሞክሮና ልምድ መቅሰማቸውን ጠቁመዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ ተመራቂዎች ስልጠናው በዘርፉ የነበራቸውን የተግባር ክፍተት የሞላ፣ ዓለም አቀፍ የገበያ መርሆዎችን በጥልቀት የተረዱበት መሆኑን ተናግረዋል።
አስተያየት የሰጠችው ናርዶስ ተክሌ እንደገለጸችው፤ ስልጠናው ከዚህ ቀደም በልምድ ላይ ተመስርታ ትሠራው የነበረውን አሠራር በሳይንሳዊ የጥራት ደረጃና በቅምሻ ዕውቀት ለመተካት እንደሚያስችላት ገልጻለች፡፡
ተመራቂ ሁሴን አህመድ በበኩሉ፤ ስልጠናው የወጪ ንግድ ሂደቶችን፣ የህግ ማዕቀፎችንና የገበያ ትስስር ስልቶችን በጥልቀት ለመረዳት እንዳስቻለው ተናግሯል።
ጋምቤላ፤ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት...
Sep 4, 2026
አሶሳ፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ተኪ ምርቶችን የማምረት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ ...
Sep 3, 2026
ሆሳዕና፤ ነሀሴ 5/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዜጎችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት መመዝገ...
Aug 12, 2026
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ)፦የመንግሥት በሙስናና ሕገ ወጥ ድርጊት የተሰማሩ አካላትን በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ርምጃ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ኢዜአ...
Aug 12, 2026