የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

ኢንስቲትዩቱ የሀገር በቀል ሀብቶች ጥበቃ ላይ በትኩረት መስራት አለበት - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)

Jan 13, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2017(ኢዜአ)፦ የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሀገር በቀል ሀብቶችና እውቀቶች ጥበቃ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች የኢንስቲትዩቱን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።


በቲማቲምና በስንዴ ምርት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም ማሽን አስተምሮት በመጠቀም አስቀድሞ የሚለይ እና ለአርሶ አደሮች ምክርን መስጠት ላይ ትኩረት ያደረገ የምርምር ውጤትን ጨምሮ በርካታ የምርምር ስራዎች ምልከታ ተደርጎባቸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያን ሁኔታ ያገናዘቡ ምርምሮችና የኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ የጀመረው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።

በምርምር ስራው የሀገር በቀል ሀብቶች ላይ የሚከሰቱ አደጋዎችን መከላከል፣ እየጠፉ የሚገኙ የሀገር በቀል እውቀቶችን መመለስ እንዲሁም የተሻለ ምርት የሚያስገኙ ዝርያዎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባው አመልክተዋል።


ኢንስቲትዩቱ ተልዕኮውን ውጤታማ ለማድረግ ከክልሎች፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትብብር እንዲያጠናክርም አሳስበዋል።

የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ካሳሁን ተስፋዬ ተቋሙ የሚሰራቸውን የምርምር ስራዎች በስፋት ለማቅረብ ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እየሰራ ነው ብለዋል።

በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአፍሪካ ደረጃ የተሻለ ስራ ለማከናወን እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ሁሉም የምርምር ተቋማት የሚጠቀሙበት የባዮ ቴክኖሎጂ እና ማቴሪያል ሳይንስ ኮር ላቦራቶሪ እንዲኖር ማድረግ እንደሚገባ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.