አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 30/2017(ኢዜአ)፦በትግራይ በክልል በ41 ቋሚና ተንቀሳቃሽ ማዕከላት ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን በኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን አስታወቀ።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ለማሳካት አስቻይ ከሆኑት ምሰሶዎች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ፣ አካታች እና በመረጃ የሚመራ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመፍጠር የሚያስችል ዋነኛ ምሰሶ መሆኑም እንዲሁ።
ፋይዳ በባዮሜትሪክ መረጃዎች ወጥ በሆነ ማንነት መታወቅ፤ መተማመን በመፍጠር አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባትም ጉልህ አንድምታ እንዳለውም ይታመናል፡፡
ኢትዮ-ቴሌኮም ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማስጀመሩ ይታወቃል፡፡
በኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ሙሉ ወልደስላሴ፤ ዲስትሪክቱ በትግራይ ክልል ባለፉት ስምንት ወራት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባን ጨምሮ የዲጂታል መታወቂያ ሕትመት አገልግሎትን በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የሰሜን ሪጅን ዲስትሪክት በ26 ቋሚና 15 ተንቀሳቃሽ ማዕከላት አገልግሎቱን በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
ደንበኞች የኩባንያውን አገልግሎት ለማግኘት ወደ ማዕከላት ሲያመሩ ብሎም በተንቀሳቃሽ ማዕከላት ባሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎቱን እንዲያገኙ በመደረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዲስትሪክቱ እስካሁን ከ235 ሺህ በላይ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፥ በቀጣይ ማዕከላቱን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሕብረተሰቡ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ያለውን ጠቀሜታ እንዲረዳ የግንዛቤ ማስጨበጭ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ነው የጠቆሙት ፡፡
በሪጅኑ በሚገኙ ማዕከላት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሲመዘገቡ ከነበሩት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወይዘሮ ራህዋ ገብረስላሴ እና ተስፈየ ገብረመስቀል፤ ብሔራዊ መታወቂያን ለባንክ አገልግሎት እንዲሁም ፓስፖርት ለማውጣት እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል፡፡
ሌሎችም ብሔራዊ መታወቂያ ለሁሉም አገልግሎት ጠቃሚ መሆኑን በመረዳት ምዝገባ ማከናወን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ሌላኛዋ ተመዝጋቢ ዮርዳኖስ ረዳ እና ወይዘሮ ለምለም ኪዳነማርያም፤ ፋይዳ መታወቂያ ህጋዊነትን ለማረጋገጥ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው፥ በመንግስትም ሆነ በግል ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ከዚህም ባለፈ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በእያንዳንዳችን እጅ መድረስ ያለበት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ተገልጋዮቹ አንስተዋል።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የማጭበርበርና ህገ ወጥ አሰራሮችን በመከላከል ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መሆኑም ይታወቃል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025