አርባ ምንጭ፤ ጥር 6/2017 (ኢዜአ)፡-የእንሰት ተክል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ከማገዝ አንጻር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አስተያየታቸውን የሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
የእንሰት ተክል ምርታማነትን በመቀነስ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ያለውን የእንሰት አጠውልግ በሽታ ለመከላከል ግብርና ሚኒስቴር የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም አስታውቋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የዘርፉ ባለሙያዎች እንደገለጹት፤ የእንሰት ተክል የምግብ ዋስትናን እንዲሁም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ አለው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ አምባሳደር ፕሮፈሰር አድማሱ ፀጋዬ እንሰት ከሌሎች የሆርቲካልቸር ሰብሎች ይልቅ ለምግብ ዋስትናና ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በሀገራችን በተለያዩ ክልሎች ቁጥሩ 20 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እንሰትን ለምግብነት እንደሚጠቀም ጠቅሰው፤ ዕሴትን ጨምሮ በማምረት የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል።
እንሰት ውሃን አምቆ ስለሚይዝ ድርቅን የመቋቋምና የመሬት ለምነትን የመጠበቅ አቅሙ የጎላ መሆኑን ተናግረው፣ ከሌሎች ምግቦች ጋር ሲታይ በንጥረ ነገር ይዘቱ የላቀ መሆኑን አስረድተዋል።
ዓመቱን ሙሉ የሚመረት፣ በምርታማነቱ ከፍተኛ የሆነና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኝ መሆኑ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንም አምባሳደር ፕሮፈሰር አድማሱ ገልጸዋል።
ተረፈ ምርቶቹ ለእንስሳት መኖነት የሚውል በመሆኑ ድርብ ጥቅም እንዳለውም አንስተዋል።
በእንሰት ላይ የተከሰተው በሽታ ለመከላከል ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብደላ ነጋሽ በበኩላቸው፤ የእንሰት ሰብል የህዝቡን የምግብ ዋስትና በማረጋገጡ ረገድ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የእንሰት አጠውልግ በሽታ በምርትና ምርታማነት ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ጫናና የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ህዝቡን ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በሽታውን ከመከላከል ባለፈ የእንሰት ዝርያን የማሻሻልና በእንሰት የሚለማን መሬት የማስፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ ወደማሳ ሲገባ ከአለባበስ ጀምሮ ተገቢ ጥንቃቄ በማድረግ የማሳ ንጽህናን በመጠበቅ በሽታውን መግታት እንዳለበት የገለጹት ደግሞ በሚኒስቴሩ የእፅዋት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይነህ ንጉሤ ናቸው።
የእንሰት ሰብል በሀገሪቱ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማና በኦሮሚያ ክልሎች በስፋት የሚመረት ሲሆን ለምግብ ዋስትናና ለውጭ ምንዛሬ የጎላ ድርሻ እንዳለው ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025