የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

<p>ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ያገኛቸውን የተሻሻሉ ምርጥ የድንችና የሰብል ዝርያዎችን ለተጠቃሚዎች ሊያሰራጭ ነው</p>

Jan 15, 2025

IDOPRESS

ሐረማያ፤ ጥር 7/2017(ኢዜአ)፡- ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ያገኛቸውንና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ ምርጥ የድንችና የሰብል ዝርያዎችን ለተጠቃሚዎች ሊያሰራጭ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።


በዩኒቨርሲቲው የኢንተርፕራይዝ ልማት ዳይሬክተር ከተማ በቀለ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የድንችና የሰብል ዝርያዎችን አባዝቷል።

ዩኒቨርሲቲው በዋናው ግቢ በሚገኘው 106 ሄክታር መሬት ላይ ያባዛቸውን የድንች፣ የበቆሎ፣ ማሽላ፣ ቦሎቄ፣ ስንዴና ሌሎች የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሰራጨት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የተሻሻሉ ዝርያዎቹን በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የማላመድ ስራ ማከናወኑንም አክለዋል።


ከምርጥ ዝርያዎቹ መካከል በተለይም 'ቡቡ' እና 'ጉደኔ' የተባሉት የድንች ዝርያዎች በሽታን በመቋቋም በሄክታር እስከ 350 ኩንታል ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

'መልካሳ 3' እና 'BH-560' የተባሉት የበቆሎ ምርጥ ዝርያዎችም በሄክታር ከ55 እስከ 60 ኩንታል መስጠት የሚችሉ እንደሆነ አስረድተዋል።

በተጨማሪም በዋናው ግቢ በሚገኘው 11 ሄክታር የምርምር መሬት ላይ የአተር ምርጥ ዘር የማባዛት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።


የዘር ብዜት ሲከናወንባቸው የቆዩና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡትን 4ሺህ 600 ኩንታል የድንች እና የሰብል ዝርያዎች በሐረሪ ክልል፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በዘር ብዜት ለተሰማሩ ማህበራትና ለአርሶ አደሩ በቅርቡ እንደሚሰራጩም ተናግረዋል።


ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 5ሺህ 230 ኩንታል የተሻሻሉ ምርጥ የድንችና እና የሰብል ዝርያዎችን በሐረሪ ክልል፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በዘር ብዜት ለተሰማሩ ማህበራትና አርሶ አደሮች ማሰራጨቱን አያይዘው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.