አዲስ አበባ ፤ ጥር 9/2017(ኢዜአ)፡- በ2016/17 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል የጥጥ ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የጥጥ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳምሶን አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ለጥጥ ልማት ቆላማ የአየር ንብረት ያላቸው አካባቢዎች ተመራጭ ናቸው።
ለአብነትም ገዋኔ፣ መተማ፣ ሑመራ፣ ጋሞ፣ ጎፋ ወላይታና ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁ ሰፋፊ የጥጥ እርሻዎች እንደሚለሙ አክለዋል።
በሀገሪቱ በ2016/17 የምርት ዘመን በ107 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጥጥ የማልማት ስራ መከናወኑን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 6ሺህ ሄክታሩ በመስኖ የለማ መሆኑን አብራርተዋል።
ከተሰበሰበው 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ጥሬ ጥጥ ውስጥ 65 በመቶ የሚሆነውን በመዳመጥ ለገበያ ዝግጁ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ዘንድሮ የተገኘው የጥጥ ምርት ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ ማሳየቱን አብራርተዋል።
ለገበያ ዝግጁ የተደረገው የተዳመጠ ጥጥ በዋናነት ለሀገር ውስጥ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች የሚቀርብ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ሳምሶን ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በቻይናና ህንድ ያሉ የጨርቃጨርቅ አምራቾች የጥጥ ምርት ጥያቄ ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለጥጥ ልማት ተስማሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ በመሆኗ ምርቱን ለማሳደግ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በተለይም አገሪቱ ለጥጥ ምርት ካላት ምቹ የአየር ጸባይና በጥጥ ሊለማ ከሚችለው መሬት አንጻር እስካሁን ከአምስት በመቶ የማይበልጠው ብቻ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል።
በዋናነት ዘርፉ በሚፈለገው መልኩ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዳያስመዘግብ ከሚያደርጉ ማነቆዎች መካከል ጥራቱን የጠበቀ የጥጥ ዘር አቅርቦት ዝቅተኛ መሆን እና ለምርት እድገት አጋዠ የሆኑ ኬሚካሎች በበቂ መልኩ ተደራሽ አለመሆን ተጠቃሽ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በተጨማሪም በዘርፉ ለተሰማሩ አምራቾች የሚደረገው ሙያዊ ድጋፍ ዝቅተኛ መሆንና የጥጥ ግብይት ስረዓቱ ላይ ያለው ህገ ወጥ አሰራር ምርትና ምርታማነቱ እንዳይጨምር ማነቆ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም አገሪቱ ከጥጥ ምርት ማግኘት ያለባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያገኘች ባለመሆኑ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ የአሰራር ስርዓቶች ተዘጋጅተው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል።
ለአብነትም በስራ ላይ የሚገኘው የ15 ዓመት ብሔራዊ የጥጥ ልማት ስትራቴጂ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስትራቴጂው ጉድለቶችን በማረም ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት የጥጥ ምርት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ላይ አገልገሎት እየሰጡ ያሉ 20 የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች መኖራቸውንና ተጨማሪ 10 ፋብሪካዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ ሳምሶን ጠቁመዋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025