የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

<p>በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ማንኛውንም አይነት ድሮን ያለ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ፈቃድ ማስነሳትም ሆነ ማብረር አይቻልም</p>

Feb 6, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ጥር 28/2017(ኢዜ)፦በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ማንኛውንም አይነት ድሮን ያለ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ፈቃድ ማስነሳትም ሆነ ማብረር እንደማይቻል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚደረግ የድሮን እና ሌሎች በራሪ አካላት አጠቃቀምን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ ተቋሙ በአዋጅ ቁጥር 1276/2014 በተሰጠው ስልጣን መሠረት የመሪዎችን፣ የቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን እና ብሔራዊ ኩነቶችን ደኅንነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት።

ተቋሙ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የመጡ ድሮኖች እና መሰል ቴክኖሎጂ ወለድ መሣሪያዎች የሚፈጥሯቸውን ስጋቶች ለመከላከል የሚያስችል በቂ የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ዝግጅት አድርጓል።

ሥራው ውጤታማ እንዲሆንም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እና ጠንካራ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንደሚፈልግ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

በተለይ ከመጪው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ጋር ተያይዞ ቅንጅቱን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ማንኛውም አይነት ድሮን ያለ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት ፈቃድ ማስነሳትም ሆነ ማብረር እንደማይቻል በመግለጫው አመልክቷል፡፡

በሥራ ምክንያት ድሮኖች መጠቀም አስፈላጊ ከሆነ ጠያቂው አካል የበረራውን ዓላማ፣ የሚበርበትን ቦታ፣ የድሮኑን አይነት እና የሞዴል ቁጥር በመጥቀስ አስቀድሞ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱን መጠየቅ እና ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባ መግለጫው አስታውቋል፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዘፈቀደ የሚነሱ እና የሚበሩ ድሮኖች ካሉ ተቋሙ አዲስ አበባንና ዙሪያዋን በጸረ-ድሮን ቴክኖሎጂ ያጠረ በመሆኑ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በማንኛውም ጊዜ ድሮኖቹን ከአየር ላይ በመለየት፣ በመጥለፍ እና ወደ አስፈላጊው ቦታ በማሳረፍ እንዲሁም የድሮን አብራሪዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ከሥራ ጋር በተያያዘ ድሮኖችን መጠቀም የሚፈልግ ማንኛውም አካል በ+251 983 00 02 98 እና +251 983 00 04 01 ስልክ ቁጥሮች በመደወል ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት እንደሚችል በመግለጫው አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.