የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

<p>ፋይዳ የዲጅታል መታወቂያ ከኢትዮጵያ ባለፈ የአፍሪካን የዲጅታል ትስስር ለማፋጠን ግብ ይዟል</p>

Feb 7, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2017(ኢዜአ)፦ ፋይዳ ከኢትዮጵያ ባለፈ በአፍሪካ የዲጅታል ትስስር፣ የፋይናንስ አካታችነትና ቀልጣፋ አገልግሎትን የማሳለጥ ግብ መያዙን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ምክትል አስተባባሪ ራሄል ይትባረክ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው "ፋይዳ ለኢትዮጵያ" የተሰኘ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።


በኢትዮጵያ የነዋሪዎችን የመታወቅ መብት ለማረጋገጥ፣ በአገልግሎት ሰጭና ተቀባዮች መካከል መተማመን እንዲዳብር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግልጽነት ተጠያቂነትና የተሳለጠ አሰራር ስርዓት ለማንበር የዲጅታል መታወቂያ ገቢራዊ ተደርጓል።

በዚህም የኢትዮጵያ ዲጅታል መታወቂያ በአዋጅ ቁጥር1284/2015 ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባ ሲሆን እስካሁን 12 ሚሊዮን ያህል ነዋሪዎች የዲጅታል መታወቂያ ባለቤት ለመሆን ተመዝግበዋል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ምክትል አስተባባሪ ራሄል ይትባረክ በዚህ ወቅት፣


ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ እንደ ስሙ ሁሉ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ዲጅታል መታወቂያ የአገልግሎት ሰጭና ተቀባዮችን በማስተሳሰር ቀልጣፋ የዲጂታል አገልግሎት መስጠት ያስችላልም ብለዋል።

ፋይዳ የዜጎችን መብት የሚያስጠብቅ፣ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅም የሚያስከብር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በ2030 በአፍሪካ የዲጅታል ትስስር፣ አካታች የፋይናንስ ስርዓትና ቀልጣፋ አገልግሎትን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ፋይዳ ዋነኛ ምሰሶ ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል።

ምክትል አስተባባሪዋ አክለውም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የፋይዳ ለኢትዮጵያ ፕሮግራም በማዘጋጀቱ ምስጋና አቅርበዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፥ ኢዜአ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ተልዕኮ የተሰጠው የሀገሪቱ የዜና ወኪል መሆኑን ገልጸዋል።

አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠሩንም ተናግረዋል።

በዚህም የዜናና ዜና ነክ ፕሮግራሞችን ከማዘጋጀት ባለፈ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ሀገራዊ ተልዕኮውን እየተወጣ ነው ብለዋል።

በብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ላይ ያተኮረው "ፋይዳ ለኢትዮጵያ" የውይይት መድረክም ፋይዳ ለሀገር ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ ያለውን ጥቅም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ኢዜአ የብሪክስ የሚዲያ ፕሬዚዲዬም አባል በመሆን ፋይዳ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊ ቀለም እንዲኖረው ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.