የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

<p>አስተዳደሩ ያሉበትን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግሮች መፍታት አለበት - ቋሚ ኮሚቴው</p>

Feb 7, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያሉበትን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግሮች መፍታት እንደሚገባው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል።

ቋሚ ኮሚቴው የአስተዳደሩን የ2017 በጀት አመት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርትና ቀጣይ ስራዎችን በተመለከተ ውይይት አካሂዷል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን(ዶ/ር) እያንዳንዱ ክልል ላይ መንገድን በበቂ ሁኔታ የማድረስ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል።


እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አዳዲስ ቴክኖሎጂን ማምጣትና መጠቀም እና አሰራሮችን ዲጂታላይዝ በማድረግ በሰው ንክኪ የሚሰሩ ስራዎችን ማስቀረት ይገባል ብለዋል።

የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋት የጋራ መሰረተ ልማቶች ሊደርሱ የሚችሉበትን ዘዴ መጠቀም፣ የተበታተነ አሰፋፈርን ሰብሰብ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ መገጣጠምያ ማቋቋም እና ለግንባታ ማሽነሪዎች ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደሚቻልም ገልፀዋል።

ከአካባቢ እና ማህበራዊ ደህንነት እንዲሁም ጤና ጋር በተያያዘም የግንባታ አካባቢዎች ለስራ ምቹ መሆን እንዳለባቸው አመላክተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በግማሽ አመት እቅድ አፈፃፀም እና በመስክ ምልከታ የተለዩ ነጥቦች ላይ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አቅርበው በአስተዳደሩ የስራ ሀላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።


የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አቡዱራህማን ተቋሙ የፕሮጀክት ምህንድስና ግዥ፣ የዲዛይን፣ የግንባታ፣ የጥገና እንዲሁም የተቋም ግንባታ ስራዎች አንጻር የ2017 ግማሽ አመት አማካይ አፈፃፀም 81 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል።

አያይዘውም ባለፉት ስድስት ወራት 55 የመንገድ ፕሮጀክቶች ግዥ፣ 30 የግንባታ ቁጥጥርና የማማከር አገልግሎት ግዥ፣ 51 የዲዛይን ስራዎች ግዥ መፈፀም መቻሉን መጠቆማቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት 10 ሺህ 633 ኪሎ ሜትር የመንገዶች ግንባታ የተካሄደ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ በመደበኛ፣ በከባድ ጥገና እና በወቅታዊ ጥገና በአጠቃላይ 17ሺህ 216 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና መከናወኑን አመላክተዋል።

የፍጥነት መንገድ እና ልዩ ግንባታ ፕሮጀክቶች አስተዳደር ላይ የመዋቅር ማስተካከያ መደረጉን፣ የራስ ኃይል የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አደረጃጀት በቦርድ የፀደቀ መሆኑን አንስተዋል።

የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት ለማጠናከር 11 ፅህፈት ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ የ4 ፅህፈት ቤቶች ግንባታቸው ሲጀመር የ1 ፅህፈት ቤት ስራ ለመጀመር ተለዋጭ ቦታ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።


በ5 ዲስትሪክቶች ላይ በስራ መደራረብ ምክንያት በዕቅዱ መሰረት መጀመር እንዳልተቻለና በ1 ዲስትሪክት ስራ ለመጀመር ከከተማ ኃላፊዎች ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የግብዓት እጥረት በተለይ ነዳጅ፣ የወሰን ማስከበር ችግር፣ በፕሮጀክት አካባቢ እንዲሁም በፕሮጀክቶች መዳረሻ(logistic corridor) የሚያጋጥሙ የፀጥታ ችግሮች፣ የጥሬ ገንዘብ እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በተለያየ ቦታ የመሬት መንሸራተት ማጋጠሙ፣ በሁሉም ፈጻሚ አካላት በኩል የሚታይ የአቅም ክፍተት በበጀት አመቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

ከሲሚንቶ ጋር በተያያዘ የተሻለ አቅርቦት መኖሩንና ችግሮች እየተቃለሉ መሆኑን፣ በፀጥታ ምክንያት የቆሙ ፕሮጀክቶች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን፣ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው እየጨመረ በመምጣቱ ባለፉት ስድስት ወራት የታዩ ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለ ለመፈፀም እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.