የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

<p>ቤት ፍላጎትን ለማሟላት ራሱን የቻለ የቤት ፋይናንስ ምንጭና አቅርቦት ለመዘርጋት ታቅዷል- የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር</p>

Feb 7, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2017(ኢዜአ)፦ የቤት ፍላጎትን ለማሟላት ራሱን የቻለ ሀገር አቀፍ የቤት ፋይናንስ ምንጭና አቅርቦት ለመዘርጋት እየሠራ መሆኑን ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት ጋር በመተባበር ባከናወነው የቤት ፋይናንስ ስርዓት ዝርጋታ ጥናት ላይ ያተኮረ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሔለን ደበበ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቤት ልማት ዘርፍ በተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ አበረታች ውጤት ተገኝቷል።

ነገር ግን በአጠቃላይ በከተሞች ካለው የቤት ፍላጎት አንጻር ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ለዚህም ከቤት ፋይናንስ፣ ከአልሚዎች፣ ከመሬት ልማት አቅርቦት ተቋማት፣ ከከተማ ፕላንና መሰል ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ ተግባር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ በቤት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ተግዳሮት ሆኖ የቆየው የቤት ፋይናንስ እጥረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ስለሆነም ተደራሽ የቤት አቅርቦትን ለማሳለጥ ራሱን ሀገር አቀፍ የቻለ የፋይናንስ ምንጭና አቅርቦት መዘርጋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ሚኒስቴሩ ሀገር አቀፍ የቤት ፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ጥናት በማከናወን ረቂቅ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

የቤት ልማት የፋይናንስ ስርዓቱ የፋይናንስ ምንጮችን መለየት፣ የቤት ልማት ፋይናንስ አቅርቦት አስተዳደር ዘዴን ማመላከት፣ ተቋማዊ መዋቅርና ስርዓትን መፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

ስርዓቱ ሲዘረጋ ለአዳዲስ ቤቶች ግንባታ፣ ለቤት ጥገናና ማሻሻያ እንዲሁም ለሌች የቤት ልማት ፕሮግራሞች የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ጠቁመዋል።

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚና የቋሚ ንብረት ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ያሳካል ነው ያሉት።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ ጸጋ በበኩላቸው፥ የተዘጋጀው የቤት ፋይናንስ ስርዓት ተግባራዊ ሲደረግ ለቤት ፈላጊዎች የቤት ችግር በመቅረፍ በኩል ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡።

ተቋሙ በቀጣይም የተለያዩ ጥናቶችንና ተሞክሮችን በማቅረብ ችግሮችን ለመፍታት የድርሻውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.