አዲስ አበባ፤ የካቲት 02/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ከጎረቤት ሀገራት አልፎ ለአፍሪካውያን ኩራትና ተስፋ የሚሰንቅ መሆኑን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ገለጹ፡፡
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም(አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ በተመለከተ ከገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ጋር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ቦርድ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ለኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ በአራት ዓመት የሚከፈል የ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር አቅርቦት ማጽደቁ ይታወሳል።
የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ህዝብ ላደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵየ ቆይታዬ የመጨረሻ ጉብኝቴ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ሙዚየሙ የአፍሪካውያን ኩራትና ተስፋ መሆኑን ተረድቻለሁ ብለዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ በማሳሰብ ጊዜው ለኢትዮጵያ ብሩህ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ የተጀመረው ሪፎርም ከግብ እንዲደርስ መተባበር እንዳለበት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንደምታስመዘግብ ባለሙሉ ተስፋ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው በመልካም ሂደት ላይ በመሆኑ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በነበራቸው የአጭር ጊዜ ቆይታ ውጤታማ ጉብኝት ማድረጋቸውን በመግለጽ፤ ኢንቨስትመንትን በመጨመር ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
የግብርናና የአገልግሎት ዘርፉ ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ መቻሉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ዓለም አቀፋዊ ችግር የሆነውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ ጥሩ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በፈጣን የለውጥ ሂደት ላይ መሆኗን በመግለጽ፤ ህዝቡ ከተሜነትን እያጣጣመ ነው ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራውን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ሪፎርሙ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የውጭ ምንሪ በገበያ እንዲወሰን በመደረጉ በመደበኛውና ትይዩ ገበያ መካከል ያለው ልዩነት እንዲጠብ ተደርጓል ብለዋል፡፡
መንግስት በሞኒተሪንግና ፊሲካል ፖሊሲ ማሻሻያዎች ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ የሚያስችል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ የክፍያ ሥርዓትን በማሻሻል እና በአረንጓዴ አሻራ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ አይ ኤም ኤፍ ለሪፎርሙ ውጤታማነት ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት መሆኗን ገልጸው፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የአይ ኤም ኤፍ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025