የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

<p>በሰብል ምርታማነት የተመዘገበው ስኬት ለአግሮ-ኢንዱስትሪ ሽግግር ምቹ መደላድል ፈጥሯል - ግብርና ሚኒስቴር</p>

Feb 11, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2017(ኢዜአ)፡- በሰብል ምርታማነት የተመዘገበው ስኬት ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በመተካት ለአግሮ-ኢንዱስትሪ ሽግግር ምቹ መደላድል መፍጠሩን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ ኢሳያስ ለማ፤ በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን በሰብል ከተሸፈነው ከ20 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት 608 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።


በእስካሁኑ ሂደትም በምርት ዘመኑ የመኸር እርሻ ሰብል 505 ሚሊየን ኩንታል ምርት 95 ከመቶ የሚሆነውን ሰብል መሰብሰብ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

በበጋ መስኖ በዚህ ዓመት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ ከ172 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት በተያዘው ዕቅድ እስካሁን 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አስረድተዋል።

የግብርና ምርታማነትን ለማስቀጠል ለሁሉም ክልሎች የበልግ፣ መኸርና መስኖ ሰብል ልማት የሚሆን የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓት እየቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የግብርና ምርታማነት የምግብ ዋስትና፣ የወጪ ንግድ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትና የስራ ዕድል ፈጠራ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስኬቶች ተመዝግቧል ብለዋል።

ለአብነትም ከዚህ ቀደም ከውጭ ይገባ የነበረን የግብርና ምርት ኢንዱስትሪ ግብዓት በራስ አቅም በመሸፈን ለአግሮ-ኢንዱስትሪ ሽግግር መሳለጥ ምቹ መደላድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መነሻነትም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ የስንዴ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተር፣ የቅባትና ጥራጥሬ ሰብሎችን በስፋትና በጥራት በማምረት ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።


የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ በሪሶ ፈይሳ፤ ለአርሶ አደሩ በተፈጠረው የገበያ ትስስር ገበያ ተኮር ምርቶችን እንዲያመርቱ በመደረጉ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

አምራችና ሸማቹን በማገናኘት የአቅርቦት ፍላጎት ላይ መሻሻል የተፈጠረበት ዕድል መኖሩንም ገልጸዋል።


የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው፤ የክልሉ የግብርና ምርታማነት በአግሮ ኢንዱስትሪ ለተሰማሩ አምራቾች የግብዓት አቅርቦት መሳለጥ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

ይህም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ የሰብል አይነቶችን በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ በጥራትና በብዛት በማምረት የአርሶ አደሩን ተነሳሽነት በማሳደግ ከፍተኛ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።


የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዓለምይርጋ ወልደሥላሴ፤ የሰብል ምርታማነት የኢንዱስትሪ ግብዓትን በማሟላትና ዋጋን በማረጋጋት የአቅርቦት ፍላጎቱ እንዲስተካከል እያደረገ ነው ብለዋል።

በ2017/18 ዓ.ም የምርት ዘመን ጥቅም ላይ የሚውል የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የግብዓት አቅርቦት ላይ በተቀናጀ ዝግጅት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴርና የየክልሎች ቢሮ ኃላፊዎቹ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.