የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

<p>የአፍሪካ ሀገራት በገቡት ቃል መሰረት ለአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል</p>

Feb 20, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2017(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ሀገራት በገቡት ቃል መሰረት ለአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ በአፍሪካ ልማት ባንክ የቀጣናዊ ውህደት ማስተባበሪያ ቢሮ ዳይሬክተር ጆይ ካቴጌከዋ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የሀገራትን የመሰረተ ልማት ትስስር በሚያሳልጡ ዘርፎች የተዋሃደች አፍሪካን ለመፍጠር የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤቱን እ.አ.አ. በ2020 በአዲስ አበባ ካደረገ ጀምሮ የአህጉሪቱን የንግድ ትስስር ለማሳለጥ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት 48 የአፍሪካ ሀገራት አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱን በማጽደቅ ከእነዚህ ውስጥ 19 የሚሆኑት የንግድ ልውውጥ ማካሄድ መጀመራቸውን የጽሕፈት ቤቱ መረጃ ያመላክታል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ የቀጣናዊ ውህደት ማስተባበሪያ ቢሮ ዳይሬክተር ጆይ ካቴጌከዋ(ዶ/ር) ባንኩ የአፍሪካውያንን የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚያግዝ ተቋም ነው ብለዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናም የሀገራትን የታሪፍ ፖሊስና ህግጋት በማስተካከል የተሰናሰለ አህጉራዊ የንግድ ሥርዓትን በመፍጠር የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመገንባት አይነተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሀገራትን የማደግ ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ በተለያዩ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የልማት መስኮች ላይ ድጋፍ በማድረግ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን እያገዘ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አህጉሪቱን በዘመነ የንግድ ሥርዓት በማስተሳሰር ያላትን ጸጋ በመጠቀም የኢኮኖሚ ዕድገቷን እንድታረጋግጥ የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ አህጉሪቱ የተሰናሰለ የንግድና ኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲኖት በሚያደርጉ የኢኮኖሚ መስኮች ላይ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በንግድና ኢኮኖሚ የተዋሃደች አፍሪካ እውን ሆና ማየት የባንኩ ተቀዳሚ ዓላማ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናም የኢኮኖሚ ውህደትን ለማሳካት ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

ሀገራትም በገቡት ቃል መሰረት አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ በማድረግ የአህጉሪቱን ዕድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ለዚህም ተለምዷዊ የንግድ ፖሊሲና አሰራርን በማሻሻል የግሉን ዘርፍ የገበያ ተወዳዳሪነት ማሳደግ በሚያስችሉ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከናወነች የምትገኘው የልማት ስራ አንድ የአፍሪካ ገበያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት አዎንታዊ ሚና የሚጫወት መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.