የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

<p>በሃዋሳ ከተማ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተፋጠነ ነው</p>

Feb 21, 2025

IDOPRESS

ሀዋሳ፤ የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፡- በሀዋሳ ከተማ በሁለተኛው ምዕራፍ እየተከናወነ ያለው የ5 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ ገለጹ።

አቶ መኩሪያ ለኢዜአ እንደገለጹት ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ የእግረኛ መንገድ፣ የብስክሌት፣ የመናፈሻ ስፍራን ጨምሮ በአንድ ጊዜ በሁለት መስመር እስከ ስድስት መኪናዎችን ማስተላለፍ የሚያስችል የአስፓልት መንገድ ሥራን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ከሀዋሳ ከተማ መግቢያ ሳውዝ ስፕሪንግ አንስቶ እስከ ፍቅር ሐይቅ እንዲሁም ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከግሎባል ጋራዥ እስከ ታቦር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ድረስ የሚከናወነው የኮሪደር ልማት ከ5 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት እንዳለውም ገልጸዋል።


ሥራውን በተቀመጠለት የስድስት ወር አጠናቆ ወደ አገልግሎት ለማስገባት ተገቢ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማት ሥራው ለየት ያለ እና አዲስ እሳቤ ይዞ መምጣቱን ጠቁመው ቀደም ሲል ከነበረው የሥራ ባህል በተለየ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ መስራት ተጀምሯል ብለዋል።

ይህን በማሳደግ ስራውን በተቀመጠለት ጊዜ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት 24 ሰዓት ለመስራት መታቀዱንም አመልክተዋል።


የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሀላፊ ኢንጂነር ምህረቱ ገብሬ በበኩላቸው፣ ሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በተያዘው ዕቅድ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የሚከናወነው የኮሪደር ልማት በመጀመሪያው ምዕራፍ ከተከናወነው ለየት የሚያደርጉት በርካታ ሥራዎች እንዳሉት ገልጸዋል።

በሐዋሳ ሐይቅ አካባቢ የሚከናወን የኮሪደር ልማት በመሆኑም ገጽታን የሚቀይርና ለቱሪዝም ምቹ የሆነ ስፍራ የሚፈጥር በመሆኑ በፍጥነትና በጥራት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ትራንስፖርት ሴክተር የሀዋሳ ኮሪደር ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ መሀንዲስ ኢንጂነር ተስፋዬ አዲስ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሆን የመሬት ቆረጣ፣ የአፈር ሥራና የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ቀበራ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።


ሥራ ተቋራጩ ሥራውን 24 ሰዓት ማከናወን ከቻለ ፕሮጀክቱን በተቀመጠለት ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቅ ይችላል ብለዋል።

በይርጋለም ኮንስትራክሽን የሀዋሳ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዮርዳኖስ ሰይፉ እንዳሉት ለስራው የሚያስፈልጉ የውሀ ማፋሰሻ ቱቦ፣ ጠጠርና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች ከስር ከስር በማምረት የማከማቸት ሥራ እየተሰራ ነው።

ተጨማሪ ማሽኖችና አስፈላጊ መሳሪያዎችን በማሟላት ሥራውን በተቀመጠለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በርብርብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.