የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

<p>የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቡና ዝርያዎችን በማልማት ተጠቃሚነታችንን ለማሳደግ እየሰራን ነው</p>

Feb 26, 2025

IDOPRESS

ዲላ፤የካቲት 18/2017(ኢዜአ)፦የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቡና ዝርያዎችን በማልማት ተጠቃሚነታውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጌዴኦ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።


በክልሉ ዘንድሮ ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ አዲስና ነባር መሬት በቡና ለመሸፈን የችግኝ ማፍላት እንዲሁም የችግኝና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።


አርሶ አደሮቹ በሽታን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቡና ዝርያዎችን እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።


ለዚህም የተፈጥሮ ማዳበሪያና የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።


ከአርሶ አደሮቹ መካከል በጌዴኦ ዞን የወናጎ ወረዳ አርሶ አደር ቤቹ አራርሶ፥ በተያዘው ዓመት በዘመናዊ የግብርና አሰራር የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለማልማት የጉድጓድ ቁፋሮና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቃቸውን አንስተዋል።


በኩታ ገጠም አንድ ሄክታር ማሳቸው ቡና በማልማት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ጠንክረው እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።


ቀደም ሲል ቡናን በተለመደው መንገድ ማልማታችን የልፋታችንን ያህል ተጠቃሚ አላደረገንም ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ አርሶ አደር ዘርፌ ባሪ ናቸው።


በተለይም ያረጁ ቡናዎች ምርታማነታቸውን እየቀነሱ በመሆኑ በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች በመተካት ልማቱን በማጠናከር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።


ለቡና ተከላ የሚሆን የጉድጓድ ቁፋሮና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ሥራ ማከናወናቸውንም ጠቁመዋል።


ከዚህ ቀደም ለቡና ልማት የተፈጥሮ ማዳበሪያ የመጠቀም ልማድ አነስተኛ እንደነበር ያነሱት ደግሞ በዞኑ የዲላ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ዳዊት ጅክሶ ናቸው።


በተያዘው ዓመትም ቡናን በመስመር ለማልማት የጉድጓድ ቁፋሮ ከማከናወናቸው ባለፈ ከቡና ተረፈ ምርት፣ ከፍግና ከተለያዩ ብስባሾች የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ በበኩላቸው፣በክልሉ በአማካይ በሄክታር የሚገኘውን 7 ኩንታል የቡና ምርት በቀጣይ ዓመት ወደ 9 ኩንታል ከፍ ለማድረግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው።


ለዚህም የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በዘመናዊ መንገድ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


በተያዘው ዓመት ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት ለመሸፈን የጉድጓድ፣የችግኝ ማፍላትና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።


ለዚህም ለተዘጋጁ ከ32 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች እንክብካቤ ከማድረግ ባለፈ ለቡና ልማት የሚውል ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል ብለዋል።


በተጨማሪም አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም በማደራጀት ለቀጣይ ተከላ የሚሆን ከ22 ሚሊዮን በላይ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.