የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

<p>በክልሉ የህብረት ሥራ ማህበራትን በማዋሃድ የአባሎቻቸውንና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው</p>

Feb 27, 2025

IDOPRESS

ቁሊቶ፤ የካቲት 19/2017(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረት ሥራ ማህበራትን በማዋሃድ የአባሎቻቸውንና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

"የተዋሃዱ ህብረት ሥራ ዩኒየኖች ለሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ የዩኒየኖች ውህደት መድረክ በክልሉ ሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ ተካሂዷል፡፡


የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጎዴቦ እንደገለጹት፣ በክልሉ የህብረት ሥራ ማህበራት የአባሎቻቸውንና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት በላቀ መልኩ እንዲያረጋግጡ የማዋሃድ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡

በክልሉ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ3 ሺህ 900 በላይ የህብረት ሥራ ማህበራት እንዳሉ ገልጸው፣ ማህበራቱ በተበጣጠሰ መንገድ ከሚሰሩ በማዋሃድ የበለጠ ተወዳዳሪና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

መዋሃዳቸው አቅም በመፍጠር በአቅርቦት ላይ ያለውን ውስንነት ከመፍታት ባለፈ ምርቶችን እሴት ጨምረው በመላክ ለኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩላቸውን እንዲጫወቱ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል፡፡


የሀላባ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀጂ ኑርዬ በበኩላቸው በዞኑ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በማቅረብ የተደራጁ የህብረት ሥራ ማህበራት ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተቃራኒው ከተነሱበት ዓላማ ውጪ በመንቀሳቀስ ለእዳ የተጋለጡ ህብረት ሥራ ማህበራት መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ውህደቱ የአባላትንም ሆነ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ማህበራቱ በተሰማሩበ መስክ አቅማቸውን አሰባስበው ለለውጥ እንዲተጉ ያስችላቸዋል ብለዋል።


የህብረት ሥራ ማህበራቱ ውህደት ተወዳዳሪ የሆኑ የህብረት ሥራ ማህበራትን መፍጠር የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጀማል ኢብራሂም ናቸው።

በዛሬው ዕለትም ሁለት የህብረት ሥራ ማህበራት በአንድ ላይ መዋሃዳቸውን ጠቅሰው ውህደቱ የነበራቸውን ሀብት በማሳደግ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ያግዛቸዋል ብለዋል።

ማህበራቱ ሲዋሃዱ ሀብታቸው ከ24 ሚሊየን 450 ሺህ ብር በላይ መድረሱንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም ህብረት ሥራ ማህበሩ የአካባቢውን አርሶ አደሮች በተለያየ መንገድ በማገዝ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ያስታወሱት ደግሞ የሀላባ ማንቼኖ ህብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኑርአህመድ ሞሳ ናቸው፡፡

በዛሬው ዕለት ከሌላ አቻ ማህበር ጋር በመዋሃድ አንድ ጠንካራ ማህበር ሆነናል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ ውህደቱ ያፈሩትን ሀብት በጋራ በመጠቀም የተሻለ ሥራ ለመስራት እድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ጨምሮ ሌሎች የክልልና የዞን የሥራ ሃላፊዎችና የህብረት ሥራ ማህበራት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.