የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

<p>የበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነታችንን በተግባር እያረጋገጠ ነው</p>

Mar 3, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፦የበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን በዳውሮ ዞን የኢሠራ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።


የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ ተከታታይነት ያለው የግብዓት አቅርቦትና የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም የዳውሮ ዞን የግብርናና አካባቢ ጥበቃ መምሪያ ገልጿል።


በዳውሮ ዞን የኢሠራ ወረዳ አርሶ አደር ዑታ በየነ፥ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ምርታማነታቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


ሌላኛው የወረዳው አርሶ አደር ወርቁ ገበየሁ፥ የበጋ መስኖ ስንዴን ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በአነስተኛ ማሳ በመለማመድ በዓመት ሶስት ጊዜ በማምረት ተጨማሪ ሃብት ማፍራት በመቻል ለውጥ እያስመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በማሳ ላይ የሚገኘው ሰብላቸውም የተሻለ ምርት መሰብሰብ በሚያስችል መልኩ በተሻለ ቁመና ላይ መሆኑን ገልጸዋል።


ግብርና ሙያተኞችም ከምርት ዝግጅት እስከ ሰብል መሰብሰብ ድረስ በበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነት ላይ ተከታታይ የቅርብ ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።


በቀጣይም መንግስት ለአርሶ አደሩ የሚያደርገውን የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና የሙያዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።


አርሶ አደሩ አየለ አመሎ የበጋ መስኖ ስንዴ በዓመት ሶስት ጊዜ የማምረት አቅምን በመፍጠር ተጠቃሚ እያደረገን ነው ብለዋል።


በዳውሮ ዞን ኢሠራ ወረዳ አሩሲ አንገላ ቀበሌ የግብርና ባለሙያ አቶ መሰለ ደበንቾ፥ ለቀበሌው አርሶ አደሮች በሚደረገው ድጋፍ በበጋ መስኖ ስንዴ በዓመት ሶስት ጊዜ የማምረት አቅም ተፈጥሯል ብለዋል።


በዳውሮ ዞን ኢሠራ ወረዳ የግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በቀለ አስፋው፥ በወረዳው 22 ቀበሌዎች 915 ሄክታር በበጋ መስኖ ስንዴ በመሸፈን በሔክታር እስከ 40 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።


የበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነትን ለማስቀጠል አንድ የግብርና ባለሙያ ለ20 አርሶ አደር የክላስተር ስምሪት በመስጠት ከማሳ መረጣና እስከሰብል ስብሰባ ድረስ የክትትልና ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


የዳውሮ ዞን የግብርናና አካባቢ ጥበቃ መምሪያ የእርሻና ሕብረት ስራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተገኝ፥ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩና ቀበሌ ግብርና ሙያተኛ የግብዓት አቅርቦት አጠቃቀምና የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


በዚህም በዞኑ በመኸር፣በበልግና መደበኛ መስኖ የሚለማ የማሳና እርሻ ሁኔታን በመለየት የግብርና ሜካናይዜሽን እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.