የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

ተደራጅተን በተሰማራንበት የሌማት ትሩፋትና የበጋ መስኖ ልማት ከራሳችን አልፎ ሌሎች መጥቀም ችለናል

Mar 10, 2025

IDOPRESS

ጎንደር/ ወልዲያ፤የካቲት 29/2017(ኢዜአ)፦በሴቶች የልማት ህብረት ተደራጅተው የተሰማሩበት የሌማት ትሩፋትና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ሌሎችንም መጥቀም መቻላቸውን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተጠቃሚ ሴቶች ተናገሩ።

የአለም የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የስኬታማ ሴቶች የስራ እንቅስቃሴ ተጎብኝቷል።

ከተጎበኙት ውስጥ በዞኑ በላይ አርማጭሆ ወረዳ በሴቶች የልማት ህብረት ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ያለው ወይዘሮ ሳባ ገብረሚካኤል አንዷ ናቸው።

ወይዘሮ ሳባ በወቅቱ በሰጡት አስተያየት፤ በሌማት ትሩፋት በሶስት ላም የጀመሩት የወተት ላም ርባታ አሁን ላይ የ19 የወተት ላሞች ባለቤት ለመሆን እንዳበቃቸው ተናግረዋል።

በየቀኑ 200 ሊትር ወተት ለጎንደር ከተማ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሆኑ ጠቅሰው፥ ለ20 ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠር መቻሏን ገልጸዋል።

ሌላዋ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አደይ መንግስቱ በበኩላቸው፥ በአንዲት ላም የጀመሩት የወተት ሀብት ልማት በአሁኑ ወቅት የሶስት ላሞች ባለቤት እንደሆኑ አስረድተዋል።

ከላሞቹም በቀን 28 ሊትር ወተት አልበው በመሸጥ በወር 18ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወይዘሮ ዘርፌ ፈረደ እንዳሉት በግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት፣ በጓሮ አትክልትና በእንስሳት ማድለብ ተሰማርተው ተጠቃሚ ሆነዋል።

ተደራጅተው የተሰማሩበት የሌማት ትሩፋትና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከራሳቸው አልፈው ሌሎችንም ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ቀኑ ቢያድጎ እንደገለጹት፥ በዞኑ 15 ወረዳዎች 21ሺህ 171 የሴቶች የልማት ህብረት ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

በልማት ህብረቱ ከ367 ሺህ በላይ ሴቶችን በአባልነት ታቅፈው በወተት ላሞች እርባታ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በንብ ማነብና በአነስተኛ ንግድ ስራዎች ተሰማርተው ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የዛሬው ጉብኝት ዓላማም በዞኑ ሞዴልና ታታሪ ሴቶችን የልምድ ልውውጥና ተሞክሮ በማካሄድ በቀጣይ ተግባሩን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት ያለመ ነው ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በሰሜን ወሎ ዞን በተካሄደ ጉብኝት ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አራጌ ይመር ባደረጉት ንግግር፥ በዞኑ የሠላም ዘላቂነት በማፅናት የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

የመርሳ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ቀለሟ ብርሃኑ፥ የሴቶች ቀንን ስናከብር በችግር ላይ የሚገኙ ሴቶችን በዘላቂነት በማቋቋም ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በመርሳ ከተማ በ32 ራስ አገዝ ማህበራት የተደራጁ ሁለት ሺህ 100 ሴቶች ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማፍራት በተዘዋዋሪ ብድር እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.