የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

የሀዋሳ የኮሪደር ልማት ሥራው በተሻለ ፍጥነት እየተከናወነ ነው

Mar 12, 2025

IDOPRESS

ሀዋሳ፤ መጋቢት 2/2017(ኢዜአ)፦የሀዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራው በተሻለ ፍጥነት ሌት ተቀን እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገለጸ።


የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በሀዋሳ እየተከናወነ ያለውን የመጀመሪያ ዙር ሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል ።

ይህም ከ5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት እንዳለው ተመልክቷል።


ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የልማት ሥራው በቀንም በማታም ፈረቃ በተሻለ ፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል።

እስከ ሰኔ ወር ባለው ጊዜ አጥጋቢ የሆነ አፈፃፀም ደረጃ ማድረስ ይቻላል ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ለሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ ውበት እያላበሳት መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ ይህ ምዕራፍ ከሀዋሳ ሐይቅ አካባቢ ጋር የሚያገናኝ መንገድና ሌሎች የመዝናኛ ሥራዎችን እንደሚያካትት ጠቁመዋል።

ልማቱ ሀዋሳ ይበልጥ ቱሪስቶችን የምትስብ ከተማ ያደርጋታልም ሲሉ ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል፡፡


የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን አስታውሰዋል።

ከተጠናቀቀው ሥራ ልምድ በመውሰድ በተሻለና ባማረ መልኩ የሁለተኛውን ምዕራፍ ሰርቶ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል ፡፡

የልማት ሥራው በተሻለ አፈፃፀም እንዲከናወን ዕለት በዕለት ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡


ሥራው በሚከናወንበት አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች የልማቱ አፈጻጸም የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የሥራው ተቋራጭ ይርጋዓለም ኮንስትራክሽን ባለቤት ኢንጂነር ዘላለም ወልደአማኑኤል፤ የኮሪደር ልማቱ የአስፋልት ፣ የእግረኛ፣ የብስክሌት መንገድና ሌሎችም ሥራዎችን ያካተተ መሆኑንና በተያዘለት ጊዜና ጥራቱን ጠብቆ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በአሁን ወቅት በከፊል የአስፋልት ማንጠፍ ሥራ ለማከናወን እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተያዘለት የጊዜ ገደብ የጥራት ደረጃው እንደተጠበቀ እንዲጠናቀቅ ሌት ተቀን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል ፡፡

በጉብኝቱ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ እና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።፡


የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.