የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

የኢትዮጵያ እና ታንዛንያ የኢነርጂ ትብብር ለቀጣናዊ ትስስር

Mar 12, 2025

IDOPRESS

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያና ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ለቀጣናዊ ትስስር፣ ለጋራ እድገትና ተጠቃሚነት ትኩረት መስጠት የዲፕሎማሲዋ አስኳል ነው።

ከቀጣናው ሀገራት ጋር ካሉ የትብብር መስኮች መካከል በኃይል መሰረተ ልማት መተሳሰር አንዱ መሆኑም ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትብብርን የሚያጠናክር እና የኢትዮጵያን ቀጣናውን በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ጽኑ ፍላጎት ማሳያ ነው።

በተጨማሪም በቀጣናው ዘላቂ የኤሌክትሪክ ገበያ ልማትን ማረጋገጥ የሚያስችል ክፍለ አሕጉራዊ ጥረትም እንደሆነ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ እና ኬንያ የሶስትዮሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት በጥር ወር 2017 ዓ.ም መፈራረማቸው ይታወሳል።

የሶስትዮሽ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር የኃይል ሽያጭ እንዲሁም ኬንያ ከታንዛንያ ጋር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ኪራይ ውልን ያካተተ ነው።

በሥምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የምታከናውን ሲሆን

የኃይል ሽያጭ ሥምምነቱ በሀገራቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ፀድቆ ከሚያዝያ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል።


የታንዛንያ የኤሌክትሪክ አቅራቢ ኩባንያ(TANESCO) በኬንያ በኩል ከኢትዮጵያ ከሚገዛው የኤሌክትሪክ ኃይል በዓመት 32 ቢሊዮን የታንዛንያ ሽልንግ (ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ) ወጪ እንደሚድን መግለጹን የሀገሪቱ ጋዜጣ ዴይሊ ኒውስ ዘገባ ያመለክታል።

ይህም በታንዛንያ በተለይም በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ያለውን የኃይል ብክነት ለመቀነስ እና የተሻለ የኤሌክትሪክ ስርጭት እንዲኖር ያስችላል ነው የተባለው።

የታንዛንያ መንግስት ዋና ቃል አቀባይ ጌርሰን ምሲግዋ ታንዛንያ አብዛኛውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቷን ከደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል እንደምታገኝ ይገልጻሉ።

በዚህም ምክንያት የኃይል አቅርቦቱን ለማድረስ ረጅም ርቀት እንደሚፈጅና የሚባክነው የኢነርጂ መጠን ሀገሪቱን በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የታንዛንያ ሽልንግ እንደሚያሳጣት አመልክተዋል።

ይህን ተከትሎ ታንዛንያ ከምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት ስርዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ወስናለች።

ታንዛንያ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የምታገኝበት ዋጋ ተመጣጣኝ እንደሆነ እና የኃይል ብክነት እና መቆራረጥን ለመቀነስ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ነው ዴይሊ ኒውስ በዘገባው ያሰፈረው።

ይህ ስምምነት የታንዛንያ ብሔራዊ የኃይል ቋትን እንደሚያረጋጋም ታምኖበታል።

የታንዛንያ መንግስት ዋና ቃል አቀባይ ጌርሰን ምሲግዋ ከዚህ ቀደም ታንዛንያ ከዛምቢያ፣ ዩጋንዳ እና ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ትገዛ እንደነበር አስታውሰዋል።

ታንዛንያ ከኢትዮጵያ የምትገዛው የኤሌክትሪክ ኃይል ከምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት መተሳሳር ጋር ተዳምሮ የኢኒርጂ ዘርፏን ለማሻሻል እና ለኢኮኖሚ እድገቷ የሚያግዝ ተአማኒነት ያለው የኃይል አቅርቦት እንዲኖራት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በዘገባው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ታንዛንያ የተፈራሙት ስምምነት ለቀጣናዊ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር ጉልህ ፋይዳ አለው።

የምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኅይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት አካል የሆነው ከኬንያ ወደ ታንዛንያ የተዘረጋው መስመር የሙከራ የኃይል አቅርቦት በታህሳስ ወር 2017 ዓ.ም መጀመሩ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.