የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

ተቋማቱ በጋራ ለመስራት የሶስትዮሽ ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

Mar 12, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2017(ኢዜአ)፦ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን እና መልቲቾይስ አፍሪካ በኪነጥበብ ዘርፍ ፈጠራዎች የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሶስትዮሽ ትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።


የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥበብና ስነጥበብ ፈጠራ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመህዲ ስምምነቱን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ኪነ-ጥበብና ስነ-ጥበብ ድንበር የሌለው የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

በጊዜና በሁኔታ የማይወሰኑ ዘመን የተሻገሩ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ቢኖሩም የኪነጥበቡ ባለቤቶች በቅጅና ተዛማጅ መብቶቻቸው በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ ሲሆኑ አይስተዋልም ብለዋል።

ይህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2010 ዓ.ም ፀድቆ ስራ ላይ በዋለው የፊልም ፖሊሲ ካስቀመጣቸው ቁልፍ የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች መካከል አንዱ የፈጠራ፣ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥሰትን መከላከል አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

ለቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ከሚሰሩ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት የዛሬው የሶስትዮሽ ትብብር ስምምነት አንዱ ማሳያ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልፀዋል።


የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር እንዳሉ ሞሲሳ በበኩላቸው የኪነ ጥበብ ስራዎች የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣት የሚቀርቡ የፈጠራ ስራዎችን ጥራት አጓድሏል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የዘርፉ ሙያተኞችና ተቋማትን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ድጋፍ እንዲያጡ እያደረገ ለስነ-ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ በጋራ መስራት የችግሩ መፍተሔ እንድንሆን ያስችላል ብለዋል።


የመልቲቾይስ አፍሪካ ግሩፕ የቁጥጥርና ኮርፖሬት ጉዳዮች ሀላፊ ኪያቤትስዌ ሞዲሞንግ(ዶ/ር) በበኩላቸው የኪነጥበቡ ባለቤቶች ተገቢውን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የአፍሪካ ተሞክሮችን በመውሰድ ለችግሩ መፍተሔ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚገኘው የበየነ መረብና የቴክኖሎጂ መስፋፋት የሰጠውን ጠቀሜታ ያህል በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ በኩል ለባለሙያውና ለኢንቨስተሩ ፈታኝ በመሆኑ የጋራ ስምምነቱ የመፍተሔ አካል እንደሚሆን ተናግረዋል።

የሶስትዮሽ የትብብር ስምምነቱ ትኩረት ግንዛቤ ለመፍጠር፣ የህግ ማሻሻያ ለማድረግ፣ መብትን ለማስጠበቅ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ህግና ስርአት ለማበጀት፣ የቴሌኮም ካምፓኒዎችን አሰራር ለማስተካከል፣ የፈጠራ ባለቤቶችን ተጠቃሚ ለማድረግና የአፍሪካን ልምድ ለመቅሰም እንደሆነ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.