ሶዶ፤ መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፡- በወላይታ ዞን በተያዘው የበጋ ወቅት ከ48 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የጓሮ አትክልቶች በመስኖ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የእርሻ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ታምሩ መለቆ እንዳሉት በዞኑ ውሀ ገብ በሆኑ አካባቢዎች በአርሶ አደሩና በማህበር በተደራጁ ወጣቶች በሁለት ዙር ከ48 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለምቷል።
በባህላዊና በዘመናዊ መስኖ የተለያዩ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬዎችን የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በፍጆታ ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማስቀረት በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ሽንኩርትና ቲማቲምን ጨምሮ የተለያዩ አትክልቶችን በባህላዊ መስኖ አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግረዋል።
በወጣቶቹ ለተደራጁ 72 ማህበራት የእርሻ መሬትና ለውሀ መሳቢያ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ፣ የአፈር ማዳበሪያና ዘር በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
በመጀመሪያ ዙር በመስኖ የለማው ምርት እየተሰበሰበ እንደሚገኝ የገለጹት ሀላፊው ሁለተኛ ዙር የመስኖ ልማትም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዞኑ የዱጉና ፋንጎ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ እስራኤል ሞታ እንዳሉት በወረዳው በበጋ መስኖ ልማት ሥራ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ፍራፍሬና ስንዴ እያለሙ ነው።
የመስኖ ልማት ለወጣቶቹ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ በአካባቢው ገበያን ለማረጋጋት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአካባቢው ገበያ ባለፈ እስከ ሀዋሳ ከተማ ድረስ በማቅረብ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በማህበር ተደራጅተው በመስኖ ልማቱ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል ወጣት መልካሙ ሀይሌ እንደገለጸው፣ በማህበሩ የታቀፉ 18 ወጣቶች በ30 ሄክታር መሬት ላይ ሽንኩርትና ቲማቲም አልምተዋል።
በመስኖ ልማት ሥራው ከራሳቸው ባለፈ እስከ 100 የቀን ሠራተኞችን ቀጥረው እያሰሩ መሆናቸውንም ነው የገለጸው።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ፀሀይነው መካሻ በበኩሉ በመስኖ ልማት ምርታማነታቸውን በማሳደግ ከገበያ ዋጋ በኪሎ እስከ አስር ብር ቅናሽ አድርገው እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግሯል።
ከመስኖ ልማቱ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውንም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025