የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

በክልሉ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ግብርናና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ እየተሰራ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

Mar 17, 2025

IDOPRESS

ባህርዳር፤ መጋቢት 7/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ግብርናና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።

የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የስታርታፕ የፈጠራ ውድድር የማጠቃለያ መርሃ ግብር በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።


ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በመድረኩ እንደገለጹት በክልሉ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት የግብርናና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ እየተሰራ ነው።

በዚህም በክልሉ የሚገነባውን ኢኮኖሚ በቴክኖሎጂና በፈጠራ ስራ በማስደገፍ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሚከናወነውን ልማትና የሚሰጠውን አገልግሎት በዲጂታል በማገዝ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ተቋምን በቢሮ ደረጃ የማቋቋምና የማጠናከር ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

በቀጣይም የበጀት አቅሙን በማሳደግና ለፈጠራ ምቹ ከባቢን በመፍጠር የመደገፍ ኃላፊነቱን የክልሉ መንግስት እንደሚወጣ ጠቁመው ዘርፉን ለደገፉ ለባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ለሌሎች አካላት ምስጋና አቅርበዋል።


በሁሉም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተወዳዳሪ የሆነች ሀገርን ለመገንባት በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ናቸው።

ወጣቶች በፈጠራና በምርምር ስራ ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

ቴክኖሎጂን በማልማት ምርታማነትን ለማሳደግ፣ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና አለም አቀፍ የስራ ዕድልን ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የቴክኖሎጂ ፈጣሪ ወጣቶችን የሚያበረታቱና ሀሳባቸውን ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችሉ ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በመከወን ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ(ዶ/ር) በበኩላቸው በወጣት የሰው ሃይልና በተፈጥሮ የታደለውን ክልል ፀጋ ለመጠቀም ቴክኖሎጂን በአግባቡ መተግበር ይገባል ነው ያሉት።

በቴክኖሎጂ የታገዙ የፈጠራ ስራዎችን በማዳበርና መረጃን በወቅቱ በማድረስ ክልሉ ያለውን ሰፊ መሬት፣ ካፒታልና የሰው ሀይል በአግባቡ ማልማት እንደሚገባም አስረድተዋል።


ፈጠራን ማህበራዊና ተቋማዊ ባህል በማድረግ ሁሉን አቀፍ እድገት ማምጣት እንደሚቻል የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ቢሮ ኃላፊ አቶ አቤል ፈለቀ ናቸው።

በመድረኩ በፈጠራ ስራቸው ተወዳድረው ከአንድ እስከ ሦስተኛ ለወጡ ወጣት የፈጠራ ባለቤቶች እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በመድረኩ የክልልና የፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የፈጣራ ስራ ባለቤት ወጣቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.