አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2017(ኢዜአ)፦ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን የበለጠ ለማሳለጥ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ሊጎለብት እንደሚገባ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
በወጪ ንግዱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ላይ ያሉ ዕድሎችና ተግዳሮቶችን በተመለከተ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የተሳተፉት አምራቾችና ላኪዎች ምርቶቻቸውን በጥራትና በብዛት ወደ ውጪ ለመላክ የመሰረተ ልማትና ያልተሳለጠ ሎጂስቲክስ አገልግሎት ክፍተት ፈጥሮብናል ብለዋል።
በተለይም ከጅቡቲ ወደብ ጋር ተያይዞ ያለው መጨናነቅና የመንገዱ ብልሽት ለተጨማሪ ወጪና እንግልት የዳረጋቸው መሆኑንም ነው ያነሱት።
መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡርን ጨምሮ የዘርፉን ተግዳሮቶች ለመፍታት የጀመራቸውን የሪፎርም ስራዎች ያደነቁት ተሳታፊዎቹ፤ ይሁን እንጂ አሁንም የዕቃ ሰነድ አያያዝ፣ ከኮንቴነር እጥረትና ከቀልጣፋ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ያልተፈቱ ተግዳሮቶች አሉ ብለዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዘርፉ የነበሩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በወሰዳቸው እርምጃዎች የወጪ ንግዱ ላይ መሻሻል መኖሩን አንስተዋል።
ሆኖም የወጪና ገቢ ምርቶች ሚዛን አለመመጣጠንን ጨምሮ በሎጂስቲክስ አቅርቦት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን አመልክተዋል።
ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስን ማቀላጠፍ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና የንግድ ሚዛኑን ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለዚህም የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር የመልቲሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰው፤ ይህም የወጪ ንግድን ለማሳደግ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ከኢትዮ-ጅቡቲ መንገድ መሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ይቀርብ የነበረውን ተደጋጋሚ የመንገድ ጥገና ጥያቄ ለመመለስም ከጅቡቲ መንግስት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የወጪ ንግዱን ወጪ ቆጣቢና ቀልጣፋ በሆነ ሎጂስቲክስ ለማሳለጥ መንግስት ከሚያከናውናቸው ተግባራት ባለፈ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፤ የባቡር አገልግሎቱን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ የወጪ ንግዱ እንዲሳለጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ተቋማቸው የወጪ ንግዱን ለማቀላጠፍ ከመሰረተ ልማት ጀምሮ ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋቱንም ተናግረዋል።
የባቡር ትራንስፖርት ቡና፣ የቁም እንሰሳት፣ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ለወጪ ንግድ ምርቶች ምቹና አስተማማኝ በመሆኑ ላኪዎች ከድርጅቱ ጋር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025