የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በማጽደቅ 48 ሃገራት ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል

Apr 3, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ጨምሮ እስካሁን 48 ሀገራት የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በማጽደቅ ለትግበራው ቁርጠኛነታቸውን ማሳየታቸውን የአህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣናው ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ ገለጹ።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና በአፍሪካ አጀንዳ 2063 የልማት ማዕቀፍ ከተያዙ ግዙፍ አህጉራዊ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ስር ከሰደደ ድህነት እንደሚያላቅቅ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና መመስረቻ ስምምነትን እ.ኤ.አ. በ2018 በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ መፈረማቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያም ስምምነቱን በወቅቱ ከመፈረም ባለፈ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል መጋቢት 12/2011 ዓ.ም አፅድቃለች።

ዋና ጸሐፊው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነቱን 48 የአህጉሪቱ አባል ሀገራት አጽድቀውታል።

እነዚህ ሀገራት ስምምነቱን ለመተግበር ያላቸውን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን የሚያሳልጡ ጠንካራ የህግ ማዕቀፎች እያዘጋጁ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ 19 አባል ሀገራት የቀረጥ መርሃ ግብር በማውጣት የንግድ ግብይት ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

አክለውም የአነስተኛና መካከለኛ አርሶ አደሮችን ምርት በማሰባሰብ አህጉራዊ የንግድ ትስስርን የሚያጠናክሩ ድርጅቶችን ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የንግድ ድርጅቶችን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረትም የአፍሪ-ኢግዚም ባንክ ለነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱ የ750 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም አስረድተዋል።

የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደትና ዕድገት በማረጋገጥ የህዝቧን ተጠቃሚነት ማጎልበት የህልውና ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቀድሞ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዬሚ ኦሲንባጆ ናቸው።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በጠንካራ የፖለቲካ አመራር መተግበር የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከአህጉራዊ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት መካከል አንዱ የሆነው ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ፤ የአፍሪካን የወደፊት የኢኮኖሚ እጣ ፋንታ የሚወስን መሆኑንም ተናግረዋል።

የአፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደትና ዕድገት የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ መታየት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለስኬቱም ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የአፍሪካን አህጉራዊ ውህደት ራዕይን እውን ለማድረግ እ.ኤ.አ በ1963 ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቋቋም ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል።

ለአብነትም የአፍሪካ መሪዎች እ.አ.አ በ2012 በአዲስ አበባ በተካሄደው የህብረቱ 18ኛ መደበኛ ጉባኤ አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና እንዲመሰረት ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎም እ.ኤ.አ በ2015 ድርድሩን በይፋ በመጀመር በ2018 አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና መመስረቻ ስምምነቱ በይፋ ተፈርሟል።

የአፍሪካ የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት 55 የአፍሪካ ሀገሮችን በአንድነት ያካተተ የነጻ ንግድ ስርዓት የፈጠረ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ስምምነት ነው፡፡

የአፍሪካ ሀገራት በአብዛኛው እቃዎች ላይ በሂደት ታሪፍን ለማስወገድ፣ የአገልግሎት ንግድን በሂደት ክፍት ለማድረግ እና የንግድ መሰናክሎችን ለማስወገድ የተስማሙበትም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.