አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማዕድን ኢንቨስትመንትና ምርታማነት ላይ እመርታዊ ለውጥ እንዲመዘገብ ማስቻሉን የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ገለጹ።
የሲሚንቶ ምርታማነት ማደጉና የግብይት ሥርዓቱም ገበያ መር መሆኑ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መነቃቃት ትልቅ አቅም እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ የማዕድን ኢንቨስትመንት ልማት ላይ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በሀገራዊ ለውጡ የተወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች በማዕድን፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪና በቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ላይ እመርታዊ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለብዝሃ ኢኮኖሚ ትኩረት መስጠቷ የዕይታና የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ በጸጋዎቿ ልክ ተጠቃሚ እንድትሆን ያስቻለ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
በማዕድን ዘርፍ የመንግስትና የግል አጋርነትን በማጠናከር በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀጣይነት ያለው የኢንቨስትመንት ልማትና ሀብትን የመለየት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የለውጡ መንግስት የማዕድን ሃብቶችን በአግባቡ በመለየት ማልማት የሚያስችል ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረጉንም አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን ተመራጭ የማዕድን ኢንቨስትመንት መዳረሻነት የሚያሳድጉ አሠራሮች እየተተገበሩ መሆኑን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ የሲሚንቶ፣ የብረት፣ የማርብልና ግራናይት የማዕድን ሃብቶች በስፋት መኖራቸውን አስረድተዋል።
በተለይም በሲሚንቶ ጥሬ ዕቃ ከሀገር ውስጥ የተሻገረ አቅም ቢኖርም፥ የኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚፈልገውን ያህል ግብዓት የማቅረብ ክፍተት እንደነበር አውስተዋል።
የለውጡ መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች አሁን ላይ የግብዓትና የፍላጎት መጣጣም መኖሩን ገልጸዋል።
በተለይም በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የለሚ ናሽናል ሲሚንቶና ሌሎች ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም እያመረቱ በመሆናቸው በገበያ መር የግብይት ሥርዓት በቂ የሲሚንቶ ምርት እየቀረበ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ይህም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በተመጣጣኝ ዋጋ የግንባታ ግብዓት እንዲያገኝና ሥራውን እንዲያቀላጥፍ አቅም ፈጥሯል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ የማዕድን ኢንቨስትመንት አልሚዎችን በመሳብ በወርቅ ምርታማነት ላይ እመርታዊ ለውጥ ማመጣቱንም ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት ለብሔራዊ ባንክ ከገባው የሚበልጥ ወርቅ በዚህ ዓመት ማስገባት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ተናግረዋል።
ይህም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የተተገበሩ የልማት ፖሊሲዎች ተረስተው የቆዩ የሀገር ሀብቶችን ለዕድገት አቅም በማዋል በኩል ትልቅ ስኬት ማምጣታቸውን ያሳያል ብለዋል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ የግብይት ሥርዓትን በማሻሻል ባህላዊ የወርቅ አምራቾችን ተጠቃሚነት በማሳደግ ምርታቸውን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርቡ እያስቻለ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ህገ-ወጥ ማዕድን የማውጣት ስራን ለመከላከልም ጥንቃቄ የተሞላበት ጠንካራ ቅንጅታዊ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት በልዩ ትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025